
ባሕርዳር: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ገለጸ። በአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ ደረጃ የቢሮው ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ በትግሉ ተስፋሁን በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ በአጠቃላይ 579 ፕሮጀክቶችን ተይዘው እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።
ለግንባታዎቹ ከክልሉ መንግሥት፣ ከፌዴራል መንገዶች ፈንድ እና ከኅብረተሰብ ተሳትፎ በድምሩ 3 ቢሊየን ብር በጀት እንደተመደበም ገልጸዋል። 90 በመቶውን ሥራም በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ መታሰቡን ጠቁመዋል።
በወረዳ አሥተዳደሮች እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ 270 ኪሎ ሜትር መንገድ አዲስ ሥራ እና ጥገና እንደሚሠራም አቶ በትግሉ አብራርተዋል። ከዚህ ውስጥም 17 የኮንክሪት ድልድዮች እና 24 የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድዮች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
ባለፉት ወራት ሰላም ባለባቸው አካባቢዎችም 117 ኪሎ ሜትር መንገድ መሠራቱን እና 1 ሺህ 948 ኪሎ ሜትር መንገድ በኅብረተሰብ ተሳትፎ መጠገኑንም አስታውቀዋል።
364 ሚሊየን ብር ከወረዳ አሥተዳደሮች እና ከኅብረተሰቡ ተሰብስቧል፤ ለ2 ሺህ 500 ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድልም በዘርፉ ተፈጥሯል ብለዋል። የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎችም ልማቱ እንዳይቋረጥ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ለመሥራት እየተሞከረ መኾኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ትኩረት መሰጠቱንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። ቢሮው ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና ከፌዴራል ባለሥልጣናት ጋር ውይይት በማድረግ በክልሉ በካሳ ክፍያ መዘግየት ያልተጠናቀቁ 61 ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ መደረሱንም የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ተናግረዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በመንገድ ግንባታው ላይም ጫና እንዳለው የገለጹት አቶ በትግሉ ችግሩን ለመፍታትም የተለያዩ አማራጮችን በመውሰድ ልማቱ እንዳይቋረጥ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡም የሚገነባው ልማት የራሱ ልማት መኾኑን በመገንዘብ በጉልበትም ይሁን በገንዘብ ግንባታው ላይ መሳተፉን እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!