
ጎንደር: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በየደረጃው ለሚገኙ የጸጥታ አመራሮች እና አባላት አቅም ለመገንባት፣ ለማጥራት እና ለማጠናከር የተዘጋጀ ግምገማዊ ሥልጠና በሦስት ክላስተሮች መስጠት ተጀምሯል።
የሚታዩ የሰላም ችግሮችን በተቀናጀ ሁኔታ ለማረም እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሥልጠናው መዘጋጀቱን የጎንደር ከተማ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አሠፋ አሸቤ ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሀይ ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እና ለማኅበረሰቡ ማኅበራዊ እረፍት ለመስጠት መሥራት እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡
ማኅበረሰቡን ወደ ልማት ለመመለስ በሥልጠናው የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ይገባልም ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፡፡
የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ከችግሩ እንዲወጣ እና ክልሉን ከውድመት ለመታደግ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ102ኛ ኮር አዛዥ እና የጎንደር ቀጣና ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ጄኔራል ዋኘው አለሜ ገልጸዋል።
ሠልጣኞች ከሥልጠናው የሚወስዱትን ግንዛቤ በተግባር በመተርጎም ዘላቂ ሰላም ሊያመጡ እንደሚገባም ነው የተብራራው።
ከሥልጠናው በኋላ በተሻለ መነሳሳት እና ቅንጅት ለሰላሙ እንደሚሠሩ ሠልጣኞቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፡- ተስፋዬ አይጠገብ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!