
ባሕር ዳር: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) “ተጽዕኖዎቹን ተቋቁመን እየሠራን ስለኾነ የግብርና ልማቱ ጨመረ እንጅ አልቀነሰም” ብለዋል።
በክልሉ 333 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 227 ሺህ ሄክታር መልማቱን ገልጸዋል።የማዳበሪያ አቅርቦቱም ከቀደምት ዓመታት በተለየ ትኩረት መሰጠቱን እና እጥረት እንዳይኖር ታልሞ እየተሠራ መኾኑን ነው ያስታወቁት። በዚህም ተግባራዊ ለውጥ እና ውጤት እየታየ እንደኾነ አብራርተዋል።
ዶክተር ድረስ ስንዴን በበጋ መስኖ 250 ሺህ ሄክታር ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 87 ሺህ 148 ሄክታር መዘራቱን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት ከታረሰው 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 160 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለመሠብሠብ ታቅዶ በቅድመ ምርት ግምገማ 145 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ መተንበዩን አስገንዝበዋል።
ከአምናው ጋር ሲነጻጸርም የ5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ጭማሪ ማሳየቱንም ተናግረዋል። በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ጫና ማሳደሩንም ጠቁመዋል።እንደ ኀላፊው ገለጻ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ በ9 ሺህ 60 ተፋሰሶች 376 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ለመሥራት ታቅዷል። እስካሁንም በ8 ዞኖች እና በሁለት የከተማ አሥተዳደሮች በ560 ቀበሌዎች ላይ የተፋሰስ ልማት ሥራው ተጀምሯል። ቀሪዎቹም በቅርብ ጊዜ ይጀምራሉም ነው ያሉት።
”በክልሉ ግጭቶች እና የሰላም መደፍረስ ቢኖርም የግብርና ልማቱ አልተቋረጠም” ያሉት ኀላፊው በአማራ ክልል የግብርና ልማቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በአግባቡ እየተከናወነ እንደኾነም ነው ኀላፊው የገለጹት።
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!