ታላላቆችን በጊዜ የሸኘው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ!

56

ባሕርዳር: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮትዲቯሩ የአፍሪካ ዋንጫ ባልተጠበቁ ውጤቶች ተመልካችን እያስደመመ የሩብ ፍጻሜ ላይ ደርሷል። ከውድድሩ መጀመር በፊት በያዙት የቡድን ሥብሥብ ለዋንጫ የተገመቱት በጊዜ ሻንጣቸውን ሸከፈው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ተገደዋል። የትም አይደርሱም የተባሉት ደግሞ መንገዳቸው ቀና ኾኖ የኮትዲቯር ቆይታቸው ተራዝሟል።

በውድድሩ ብዙ እንደሚራመዱ የተገመቱት አልጀሪያ፣ ጋና እና ቱኒዚያ ከምድብ ማለፍ አለመቻላቸው የእግር ኳስን አይገመቴነት ያሳየ ነው። እነዚህ ቡድኖች አንድም ጨዋታ ማሸነፋ ሳይችሉ ነው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት። በአንጻሩ ብዙ ግምት ያላገኙት ኬፕ ቬርዴ፣ አንጎላና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ ሀገራት በውድድሩ መድመቃቸውን ቀጥለዋል። ሞሪታኒያ እና ናምቢያን የመሳሰሉ ብዙ ስም የሌላቸው ሀገራት ጥሎ ማለፉን መቀላቀላቸውም በአህጉሩ የእግር ኳስ ደረጃ ልዩነት መጥበቡን ማሳያ ነው።

የባለፈው የውድድሩ አሸናፊ ሴኔጋል ዘንድሮም ዋንጫውን የማግኘት ቅድመ ግምት አግኝታ ነበር። ከግብ ጠባቂ አስከ አጥቂ በተለያዩ የዓለማችን ታላላቅ ክለቦች የሚጫወቱ ኮከቦች ባለቤትም ናት። ውድድሩ ሲጀመርም አሳማኝ ብቃት አሳይታ የተሰጣት ግምት ትክክል መኾኑን አሳይታለች።

በምድቡ ሦስቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ብቸኛ የኾነችው የሴኔጋል ቡድን በጥሎ ማለፉ ጨዋታ በአዘጋጇእና ወድቃ በተነሳችው ኮትዲቯር ተሸንፋለች። በምድቡ ሴኔጋል ካሳየችው ጥንካሬ እና የኮትዲቫር ተንጠልጥሎ ማለፍ ሲታሰብ የነ ማኔዋ ሀገር በቀላሉ እንደምታሸንፍ ግምት አግኝታ ነበር። ነገር ግን ግምቱ እውን ሳይኾን ቀርቶ የኮከቦች ሀገር ሴኔጋል ከውድድሩ ተሰናብታለች።

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ በመድረስ የአፍሪካ ኩራቷ ሞሮኮ ሌላኛዋ የዚህ ውድድር ውርደት ገፈት ቀማሽ ኾናለች። በፊፋ የሀገራት ደረጃ መሰረት ሀገሪቱ የወቅቱ የአፍሪካ ቁጥር አንድም ናት፡፡

ይህን ዋንጫ ለማንሳት ከሞሮኮ የተሻለ ቡድን የለም የሚለው የብዙዎች ሀሳብ ነበር። በምድብ ጨዋታዎች ያን ያህል ፈታኝ ቡድን ባይገጥመውም ያለሽንፈት የምድቡ የበላይ ኾኖም አጠናቋል ይህ ቡድን።

በጥሎ ማለፋ ብሔራዊ ቡድኗ ብዙም ከማይወራለት ደቡብ አፍሪካ ጋር መገኘቷም ለረጅሙ መንገዷ መሰናክሏ እንደሚቀልላት ታስቦ ነበር። ነገር ግን የማንዴላዋ ሀገር ሞሮኮን በማሸነፍ ግስጋሴዋን ቀጥላለች።

የሞሀመድ ሳላዋ ግብጽ በውድድሩ ብዙ ተጠብቃ በልኳ ያልተገኘች ሌላዋ ሀገር ናት።ግብጽ በአፍሪካ ዋንጫ የሚያኮራ ታሪክ ባለቤት፤ ዋንጫውን ብዙ ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚዋ ሀገር ናት።
ነገርግን በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ደካማ ኾና ታይታለች። የምድብ ጨዋታዎቿን ሁሉንም አቻ ስታጠናቅቅ በጥሎ ማለፍም በኮንጎ በመለያ ምት ተረታለች።

34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እነዚህን ጨምሮ ካሜሮንን የመሳሰሉ ትልልቅ ቡድኖችን በጊዜ ሸኝቷል። ምንም እንኳ አሁን በውድድሩ ውስጥ ብትገኝም አዘጋጇ ኮትዲቯር በምድብ ጨዋታዎች ያሳየችው አቋም ትዝብት ላይ ጥሏታል።

የኮትዲቯሩ ዝግጅት በእስካሁን ጉዞው ቡድኖች የተሻለ ተፎፎካሪነት ያሳዩበት ኾኗል። ትልቅ እና ትንሽ በተባሉ ቡድኖች የሰፋ ልዩነት አልታየም። ይልቁንም ለዋንጫ የታጩ ቀዳሚ ቡድኖች በጊዜ ከውድድሩ ተሰናበቱ እንጅ።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም የሚመጣው በጋራ ሲሠራ ነው” ኮሎኔል ወርቁ አሸናፊ
Next article”በክልሉ ግጭት እና የሰላም መደፍረስ ቢኖርም የግብርና ልማቱ አልተቋረጠም” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)