
ደብረ ታቦር: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)”ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ ለደቡብ ጎንደር ዞን እና ለደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የጸጥታ ኀይሎች ሥልጠና መሰጠት ተጀምሯል። ሥልጠናው ወቅታዊ ጉዳዮችን በውል በመለየት ለቀጣይ ተልእኮ ለመዘጋጀት አስተዋጽኦ እንዳለው ተመላክቷል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ባደረጉት ተጋድሎ ከተማዋ ሰላማዊ እንድትኾን ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ቀጣይ ሥራዎችን በተገቢው በመገምገም ከሰላም ወዳዱ ሕዝብ ጋር ለመሥራት መወያየት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት።
በከተማዋ የነበረው የሰላም እጦት የልማት እንቅስቃሴውን አቁሞት እንደነበርም ከንቲባው አስታውሰዋል። የልማት እንቅስቃሴው መቆም ደግሞ የከተማዋን ነዋሪዎች በእጅጉ እንዲጎዱ አድርጓቸዋል ነው ያሉት። የሰላም አለመኖር የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር እና ለወጣቶች የሥራ እድል እንዳይፈጠር ማድረጉንም ተናግረዋል።
በሥልጠናው የሚገኘውን እድል እና ወኔ በመውሰድ በወኔ ከተነሳን እስካሁን ያመለጡንን የልማት ሥራዎች በቀሪ ጊዜያት ማካካስ እንችላለን ነው ያሉት። የሕዝቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማስተካከል እና የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል ከጸጥታ ኃይሉ ይጠበቃልም ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ102ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ወርቁ አሸናፊ የተጀመረውን ሰላም እና ልማት ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ሰላም እንዲመጣ ከሕዝብ ጋር በመኾን መሠራታቸውንም ገልጸዋል። አሁንም የቀሩ የሰላም እጥረቶችን ለመፍታት እና ማኅበረሰቡን ወደ ልማት እንዲዞር ለማድረግ በአንድነት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ክልሉ የጸጥታውን ሥራ በራሱ እንዲሠራ እየተመቻቸ መኾኑንም ገልጸዋል። ሥልጠናው ወቅታዊ ሁኔታውን ለመረዳት፣ የነበረውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል፣ በአስተሳሰብ አንድ ለማድረግ እና ለሰላም ለመሥራት ያስችላል ነው ያሉት።
ከመንደር ያልተፈጠረ ሰላም በሀገር ደረጃም ሊፈጠር አይችልም ያሉት ኮሎኔል ወርቁ “ሰላም የሚመጣው በጋራ ሲሠራ ነው” ብለዋል። ሰላሙን ከሥር ጀምሮ ማጽናት ይገባልም ብለዋል።
በተሠራው ሥራ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ለሰላም እየገቡ እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር አብረው እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። አሁንም ለሰላም ያልገቡ ኃይሎችን ለሰላም እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአካባቢው የጸጥታ ኃይል አካባቢውን ሲጠብቅ የመከላከያ ሠራዊት ለሌላ ሀገራዊ ተልዕኮ ራሱን ያዘጋጃልም ነው ያሉት። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሲጠነክር ሀገር እንዳትደፈር እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ በከፍታ አስበን ሀገርን ከፍ ሊያደርግ የሚችል ሥራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ሥልጠናው ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የሚያስችል መኾኑንም ተናግረዋል።
የጸጥታ ኃይሎች ሥልጠናውን በተገቢው መንገድ በመውሰድ በሃሰት እና በስሜት የተፈጠረውን ግርግር በማስቆም ሰላምን እንዲያጸኑም አሳስበዋል። የጸጥታ ኃይሎች ሰላም አንዲታጣ ባደረጉ ጉዳዮች ላይ መምከር እና መፍትሔ ማስቀመጥ አለባቸው ነው ያሉት።
ሰላም እና ልማት ለሚፈልገው ሕዝብ ልንደርስለት ይገባልም ብለዋል። መንግሥት ለሰላም ቁርጠኛ መኾኑን ያነሱት አቶ ጥላሁን ገብቷቸው ይሁን ሳይገባቸው የአካባቢውን ሰላም እንዲደፈርስ እየተሳተፉ ያሉ ኃይሎችን የሰላም አማራጭን እንዲጠቀሙ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በሥልጠናው እየተሳተፉ የሚገኙ የጸጥታ ኃይሎችም ሥልጠናው በቀጣይ ለሚኖራቸው ግዳጅ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ሥልጠናው አመለካከትን በመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት። በሥልጠናው ያገኙትን ግብዓት በመጠቀም ሰላም ለማስፈን እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!