የመሬት አያያዝ ክፍተቶችን በመለየት እና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።

14

ደሴ: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአማራ ክልል መሬት ቢሮ እና ከአማራ ክልል ምክር ቤት ጋር በመተባበር በገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በደሴ ከተማ ምክክር እያካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ “መሬት የሁላችንም ሃብት በመኾኑ የመሬት አያያዝ ክፍተቶችን መለየት እና የተደራጁ መረጃዎችን በማሠባሠብ መሥራት ይገባል ብለዋል።

በክልሉ መረጃን በማዛባት የአቅመ ደካሞችን እና የሴቶችን መሬት የመቀማት አዝማሚያ ይስተዋላል ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለይቶ ወቅቱን የዋጀ የመረጃ አያያዝ በመፍጠር መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የመሬት አጠቃቀም አዋጁን መቃኘት እና ዘመኑን የዋጀ አሠራር ማስቀመጥ ያስፈልጋል ያሉት አፈ ጉባኤዋ በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን በማጥራት ለሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

ከሚሠሩ የልማት ሥራዎች ባሻገርም የክልሉን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ውይይቶችን በማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ምክክሩ 18 ዓመት ያስቆጠረውን የሀገሪቷን የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ላይ የወጣውን የመሬት አዋጅ ቁጥር 456/1997 ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው ትኩረት ያደረገው።

በምክክሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ አባላት፣ የክልል እና የዞን የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ነው።

ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሞሀ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ በአዲስ አሠራር ወደ ሥራ ሊገባ መኾኑን አስታወቀ።
Next articleየተዛባ አስተሳሰብን በሥልጠና በማስተካከል የሕግ ማስከበር ተግባራቸውን እንደሚወጡ የጸጥታ አባላት ተናገሩ፡፡