
አዲስ አበባ: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለአራት ወራት ሥራ አቁሞ የነበረው ሞሀ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ወደ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩብ በመቀላቀል አዲስ ሥርዓትን አዋቅሮ ወደ ሥራ ሊገባ መኾኑን የሚድሮክ የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ኀላፊ ሰዒድ ሙሐመድ ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪው 45ኛ የሚድሮክ የማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ኾኖ እንደሚሠራ ነው አቶ ሰዒድ ያብራሩት። ተቋርጦ የነበረውን ምርት በአዳዲስ የለስላሳ መጠጦች በጥራት እና በብዛት በማምረት ወደ ሕዝቡ እንዲደርስ እንደሚደረግም አስገንዝበዋል።
ኢንዱስትሪው ከፔፕሲኮ ጋር ተቀናጅቶ ሊሠራ መኾኑንም ኀላፊው ጠቅሰው ለአዳዲስ ሠራተኞች የሥራ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ሞሀ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪም በሀገር ውስጥ ስምንት ፋብሪካዎች ያሉት መኾኑ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ራሄል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!