ትምህርት ሚኒስቴር በሰሜኑ ጦርነት ወድሞ የነበረውን የዘናልቃ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመልሶ ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት አደረገ።

16

አዲስ አበባ: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ትምህርት ሚኒስቴር በሰሜኑ ጦርነት የወደመውን የድሃና ወረዳ ዘናልቃ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በመልሶ ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ አሥተዳዳሪን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የድሃና ወረዳ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የዘናልቃ ቀበሌ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ “ትምህርት ሚኒስትር ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን በብሔረሰብ አሥተዳደራችን መገንባቱ ለአካባቢው የሰጠውን ትኩረት ያሳያል” ብለዋል።

በቀጣይም የትምህርት ቁሳቁሶችን እና መሰል ግብዓቶችን ለማሟላት ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በትኩረት ይሠራልም ነው ያሉት።

ቄስ አማረ ውበት ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት ትምህርት ቤቱ በጦርነቱ በመውደሙ ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀው መቆየታቸውን አስገንዝበዋል፡፡”አሁን ግን እንኳን ልጆቻችን እኛም እንድንማር የሚያነሳሳ ነው” ብለዋል።

የትምህርት ቤቱን ግብዓቶች ለመጠበቅ እና በትምህርታቸውም ውጤታማ ለመኾን መዘጋጀታቸውን የዘናልቃ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አጸደ ግርማይ እና ተማሪ አትክልት በየነ ተናግረዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ላደረገው ድጋፍ በድሃና ወረዳ ሕዝብ ስም ምሥጋና ያቀረቡት የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሃም ተቀባ ናቸው። ትምህርት ቤቱ ሦስት ሕንጻ ያለው ሲኾን 10 የመማሪያ ክፍሎች እና ሁለት ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶችን ያካተተ ነው፡፡ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ትምህርት ሚኒስቴር ወጭ እንዳደረገበትም ኀላፊው አብራርተዋል።
የቀበሌው ነዋሪ ልጆቻቸውን በማስተማር እና የትምህርት ቤቱን አጥር በመገንባት የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article4 ሺህ 493 የሳይቨር ጥቃት ሙከራዎች ማክሸፍ መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleሞሀ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ በአዲስ አሠራር ወደ ሥራ ሊገባ መኾኑን አስታወቀ።