
አዲስ አበባ: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፉት ስድስት ወራት 4 ሺህ 623 አጠቃላይ የሳይቨር ጥቃት ሙከራዎች የተደረጉ ሲኾን 4 ሺህ 493 የጥቃት ሙከራዎችን ማክሸፍ መቻሉም ተገልጿል። በዚህም በሀገሪቱ ሊደርስ የሚችልን ከ10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ማዳን ተችሏል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ በ2016 የበጀት ዓመት አጋማሽ ተቋሙ ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ከተደረጉት የሳይቨር ጥቃቶች ወደ 98 ነጥብ 56 በመቶ የሚኾነውን ማክሸፍ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የመሠረተ ልማት ማቋረጥ፣ አገልግሎት ማቋረጥ፣ ዳታዎችን መስረቅ፣ የግንኙነት መንገዶችን መጥለፍ እና ገንዘብ ማጭበርበር ሊደርሱ የነበሩ የሳይበር ጥቃት ዓይነቶች ናቸው ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት ዋነኛ የጥቃት ኢላማ ነበሩ ነው ያሉት። በተጨማሪ የጸጥታ ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት እና የመንግሥት ተቋማት የጥቃት ሙከራ ተደርጎባቸዋል ተብሏል።
በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ከሁለቱም ቴሌኮም ኦፕሬተሮች ጋር በጋራ በመኾን በሠራው የሲምቦክስ ጥቃት አዲስ አበባን ጨምሮ በሰባት ከተሞች 43 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።
ከ200 ሺህ በላይ የሳፋሪኮም እና የኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርዶችን መያዝ ተችሏል። በዚህም በአጠቃላይ ወደ 450 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።በተጨማሪ ተቋሙ በሰባት ተቋማት ላይ የሳይበር ደኅንነት አደጋ ፍተሻ ማድረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ሰለሞን ሶካ ተናግረዋል።
ተቋሙ ሊደርሱ የነበሩ የሳይቨር ጥቃቶችን በማስቀረት፣ የደረሱ ጥቃቶችን በማስቆም፣ አደገኛ የደኅንነት ስጋት ሊደቅኑ የሚችሉ ቴክኖሎጅዎችን በመቆጣጠር ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ማዳን ተችሏል ነው የተባለው።
ዋና ዳይሬክተሩ የከሸፉ የሳይቨር ጥቃቶቹ ተሳክተው ቢኾን ኖሮ በግለሰብ፣ በተቋማት እና በሀገር ምጣኔ ሃብት፣ ፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲ እና የሥነ-ልቦናዊ ኪሳራ ያስከትሉ ነበር ሲሉም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!