
ደብረ ብርሃን: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የጸጥታ ኀይሉን ለማጠናከር ያለመ ወቅታዊ ግምገማዊ የሥልጠና መድረክ እየተካሄደ ነው።
ሥልጠናው ከጥር 22/2016 ዓ.ም እስከ የካቲት 1/2016 ዓ.ም ለተከታታይ 10 ቀናት ይቆያል።
በመድረኩ ላይ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮማንዶ እና አየር ወለድ ምክትል አዛዥ እንዲሁም የሸዋ ኮማንድ ፖስት ምክትል ሠብሣቢ ብርጋዴር ጄኔራል አበባው ሰይድ ተገኝተዋል።
ሥልጠናው በመላው አማራ ክልል የሚካሄድ መኾኑንም ብርጋዴር ጄኔራሉ ተናግረዋል።
እስካሁን የጸጥታ ኀይሉ በደብረ ብርሃን ከተማ እና አካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ላደረገው አስተዋጽኦ አመሥግነዋል።
በሥልጠና መድረኩ ላይ የተገኙት የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት “የጸጥታ ኀይሉ በቅንጅት ባደረገው ተሳትፎ ከተማዋ አንፃራዊ ሰላም ላይ ናት” ብለዋል።የከተማዋ ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው ሥልጠናው ወሳኝ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ዮናስ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!