ልድያ ዩኒቨርሲቲ ከወልድያ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ለ10 ቀናት የሚቆይ የቀዶ ጥገና ሕክምና ዘመቻ እየሰጠ ነው።

9

ወልድያ: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ክፍል ከዩኒቨርሲቲው የህክምና ኮሌጅ መምህራን እና ከወልድያ ሆስፒታል ጋር በመቀናጀት ለ10 ቀናት የሚቆይ የቀዶ ጥገና ህክምና እየሰጠ ነው።

ህክምናው ከሆስፒታሉ ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው የትምህርት እና ምርምር ምክትል ኘሬዚደንት ሱልጣን ሙሐመድ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው እስከ 5 ሚሊዮን ብር መድቦ ህክምናው እንዲሰጥ እያደረገ ነው ብለዋል።

ለ10 ቀናት የሚቆየው የህክምና ዘመቻ የተለያየ በሽታ ያለባቸው እና ሆስፒታሉ ለቀዶ ጥገና ቀጠሮ ከሰጣቸው ህሙማን መካከል ከ150 በላይ የኾኑትን ለማከም መታቀዱን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የላብራቶሪ ህክምና ክፍል ኀላፊ እና የዘመቻው አስተባባሪ ዘላለም ደጃዝማች ገልጸዋል

የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ፍስሀ የኋላ አንድ ታካሚ የቀዶ ጥገና ቀጠሮ በተሰጠው በ14 ቀናት ውስጥ መታከም እንዳለበት የህክምና መመሪያ ቢኾንም የታካሚው ቁጥር ከፍተኛ መኾን፣ የሠራተኛ ማነስ እና የገንዘብ አቅም ህሙማን ለአንድ ዓመት ያክል በቀጠሮ እንዲጉላሉ ኾነዋል ነው ያሉት።

አቶ ፍስሃ ዘመቻው የሆስፒታሉን የሥራ ጫና በማቃለሉም ቀዶ ጥገና የሚፈልጉ ቀጣይ ታካሚዎች የቀጠሮ ጊዜ ሳይራዘም ባፋጣኝ እንዲታከሙ ያደርጋልም ብለዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው ታካሚዎች ለዓመታት በቀጠሮ ሲጉላሉ መቆየታቸውን ገልጸው ድንገት ለህክምና ሲጠሩ እንደተደሰቱ ነግረውናል።

በህክምናውም ዘላቂ ፈውስ ከማግኘታቸው ባሻገር እስካሁን ሲያወጡት ከነበረው የመድኃኒት ግዥ ወጭ በመገላገላቸውም ዩኒቨርሲቲውን አመሥግነዋል።

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተቋቁሞ ጠንካራ የግብርና ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
Next article“የጸጥታ ኀይሉ በቅንጅት ባደረገው ተሳትፎ ደብረ ብርሃን አንፃራዊ ሰላም ላይ ናት” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት