
ባሕር ዳር: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ተቋቁሞ ጠንካራ የግብርና ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማት የ2016 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የሥራ ክንውን በባሕር ዳር ቀርቦ ተገምግሟል። በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር) ግብና የሕዝብ እና የሀገር የህልውና ጉዳይ በመኾኑ በየትኛውም ሁኔታ መቋረጥ የሌለበት ሥራ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል።
በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር የግብርና ሥራውን እንደልብ ተዘዋውሮ በመደገፍ በኩል ክፍተት ቢፈጥርም አማራጭ የግንኙነት ዘዴዎች ተፈጥረው ሥራውን ለማከናወን ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
ዶክተር ድረስ የክልሉን የግብርና ሥራ በማዘመን ኹነኛ የምጣኔ ሃብታዊ አማራጭ ለማድረግ ታልሞ እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል። ግብርናውን ለማዘመን በጥናት ላይ የተመሰረተ የግብርና ምርምር የአሠራር ለውጥ ተዘጋጅቷል፤ ይህም እስከታችኛው የግብርና መዋቅር ወርዶ ይተገበራል ብለዋል።
ጠንካራ ተግባቦት እና አሠራር በመዘርጋት የግብርና ሥራው ችግሮች ተቀርፈው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ እየተሠራ ስለመኾኑም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።
ኀላፊው የሕልውና መሠረት የኾነውን የግብርና ሥራን ጭምር ሲፈትን የነበረው የጸጥታ ችግር አሁን ላይ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል። ቢሮው የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ተጠቅሞ እስከ አርሶ አደሩ ድረስ እየወረደ ሥራውን በውጤታማነት ለመፈጸም እድል ማግኘቱን አመላክተዋል።
የግብርና ቢሮው እና የተጠሪ ተቋማቶቹ የግማሽ ዓመት የሥራ እንቅስቃሴ ጥንካሬ፣ ውስንነት እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች በመድረኩ ላይ ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!