“ጥር 23 አይቀርም፤ እንጀባራም እንግዶቿን አዲናስ ብላ ለመቀበል ዝግጅቷን ጨርሳለች” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)

25

ባሕር ዳር: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአገው ሕዝብ የጀግንነት እና የአርበኝነት ምልክት የኾነው 84ተኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ ክብረ በዓል በእንጀባራ ከተማ ጥር 23/2016 ዓ.ም በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የበዓሉን ታሪካዊ እና ማኀበራዊ ፋይዳ አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል። ዶክተር መንገሻ ፈንታው ዓመታዊው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ማኅበራዊ እሴቱን በጠበቀና ለቱሪዝም መስህብ በሚኾን አግባብ በድምቀት ይከበራል ብለዋል።

ኀላፊው በመልእክታቸው ቀደምት ጀግኖች አባት አርበኞች በሙሉ የኢትዮጵያን ነጻነት፣ ሉዓዋላዊነት እና ዳር ድንበር ለማስከበር ሲሉ የከፈሉት መስዋዕትነት ምንግዜም በታሪክ የሚዘክር ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለውታል።

የአገው ሕዝብ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት ለሀገር ሉዓላዊነት ሲል ከፈረሶቹ ጋር ተዋግቷል፤ ለነፃነት ዘምቷል፤ በተጋድሎውም አኩሪ ታሪክ ሰርቷል። ይኽ ታሪካዊ ክስተት በአገው ፈረሰኞች ማኅበር ፊት አውራሪነት ሲዘከርይኖራል።

ዓመታዊ ክብረ በዓሉ የአርበኛ እናቶቻችንን እና አባቶቻችንን ጀግንነት ከማክበር ባለፈ በጦር ሜዳ አኩሪ ተጋድሎዎች ውስጥ ከአርበኞቻችን ጋር አብረው የዘመቱ ፈረሶች ለሀገር የሰጡትን አገልግሎት እና የከፈሉትን መስዋዕትነት ለማስታወስ እና ለመዘከር ታልሞ ነው፡፡

የአገው ሕዝብ ለሀገር አንድነት ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት ከማረጋገጡ ባሻገር፤ ለኢትዮጵያ ህልውና ሲባል የተከፈለን ዋጋ የማይረሳ እና ውለታ ከፋይ የኾነ አመስጋኝ ሕዝብ መኾኑንም ጭምር ያሳያል፤ ፈረስ ለአገው ሕዝብ ሁለተናዊው ነገር ነው።

ፈረስ በአገው ሕዝብ ዘንድ የአርበኝነት እና የጀግንነት ምልክት ብቻ ሳይኾን የእለት ከእለት ኑሮ መስተጋብር አጋዥ፣ የእርሻ እና የትራንስፖርት መሳሪያም ጭምር ነው። በመኾኑም በአገው ማኅበረሰብ ዘንድ ፈረስ ሁሉ ነገሩ ነው።

የአገው ሕዝብ እና ፈረስ ለዘመናት የጸና እና የተለየ ቁርኝት አላቸው። በዚህ የተነሳ በዓሉን የአገው ሕዝብ በሚታወቅበት ባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች አሸብርቆ፤ በጃኖ ደምቆ በፈረስ ጉግሣ ትርኢት ይከበራል።

በዓሉ መነሻውን የተጋድሎ ታሪክ እና ሀገራዊ ድልን ታሳቢ በማድረግ ላለፉት 83 ዓመታት በአገው ፈረሰኞች ማኅበር አስተባባሪነት ሲከበር ቆይቷል። ዘንድሮም በልዩ ልዩ ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች ታጀቦ የአገው ሕዝብ የጀግንነት እና የአርበኝነት ምልክት የኾነው 84ኛው ዓመታዊ ክብረ በዓልን በታላቅ ድምቀት ለማክበር አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀዋል።

የበዓሉ መንፈስ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በኢትዮጲያዊነት መንፈስ የሚያስተሳስር፣ ዘመን እና ትውልድን የሚሻገር በመኾኑ የሀገር ፍቅር ነበልባል በሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ እንዲበራ ያግዛል።

ዶክተር መንገሻ በመልእክታቸው በዜጎች መካከል አንድነት እንዲጠናከር፣ ሰላም እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲስፋፋ፣ እርስ በርስ የመከባበር እና የእኩልነት እሴትን የሚያበረታ በመኾኑ 84ተኛ ዓመቱ ክብረ በዓል ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ እንዲከበር የሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል አዎንታዊ አስተዋጽዖ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

“ጥር 23 አይቀርም፤ እንጀባራም እንግዶቿን አዲናስ ብላ ለመቀበል ዝግጅቷን ጨርሳለች” ያሉት ዶክተር መንገሻ እንኳን ለ84ተኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ ክብረ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”የማዳበሪያ አቅርቦት እንዳይዘገይ ሕዝቡ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleየተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተቋቁሞ ጠንካራ የግብርና ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።