”የማዳበሪያ አቅርቦት እንዳይዘገይ ሕዝቡ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

24

ባሕር ዳር: ጥር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የግብርናው ዘርፍ በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ለማቅረብ እና ኤክስፖርት ለማድረግ ታሳቢ አድርጎ እየሰራ መኾኑን ዶክተር ድረስ ገልጸዋል። የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራንም ጎን ለጎን እየሰራ ነው ብለዋል።

ዶክተር ድረስ እንዳሉት ከ85 በመቶ በላይ በግብርና ለሚተዳደር ሕዝብ ዘርፉ ከማምረት በላይ ነው ብለን ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው። ሰብል ማምረት፣ የእንስሳት እርባታ እና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራዎች የትኩረት መስኮች እንደኾኑም ጠቁመዋል።

በክልሉ የተከሰሠተው የሰላም እጦት በግብርናው ዘርፍ ላይ ተጽዕኖ አሣድሯል፤ ጉዳትም አስከትሏል ያሉት ኀላፊው ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ እስካሁን ያለው የሰላም እጦት ንብረት እያወደመ መኾኑን እና እንደልብ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ማስቸገሩን እንደ ፈታኝ ሁኔታ አንስተዋል።

የሰላም እጦቱ በተለይም በመስኖ እና በተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራዎች ላይ ውስንነቶችን መፍጠሩንም ጠቁመዋል። ከባለሙያዎች ጋር የስልክ ግንኙነት በማድረግ ለመምራት እና ለማገዝ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ነው ኀላፊው ያነሱት።

”የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥያቄ የተነጠለ አይደለም” ያሉት ዶክተር ድረስ ሳህሉ ጥያቄዎቻችን ማቅረብ ያለብን በሰላማዊ መንገድ እንጂ በሁከት መኾን የለበትም ብለዋል። ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገቡ እና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቁት አፍራሽ ጉዳዮችን እየተከተሉ ሕዝብን መረበሽ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

”ግብርናችንን ለማልማት እና ለማዘመን ሰላም መሠረታዊ ነገር ነው” ያሉት ኀላፊው የክልሉ መንግሥትም ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ መኾኑን አንስተዋል። ያለፈው ምርት ዘመን የማዳበሪያ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከጥቅምት ጀምሮ መቅረብ ጀምሯል ነው ያሉት።

8 ነጥብ 05 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙንም ተናግረዋል። 2 ነጥብ 6 ሚሊየኑ ከወደብ ወደ ክልሉ መግባቱን እና አምና በዚህ ወቅት ከገባው በ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ብልጫ እንዳለው አብራርተዋል።

ቀሪውን ማዳበሪያ በፍጥነት ለማጓጓዝም ሰላም አስፈላጊ መኾኑን የጠቀሱት ዶክተር ድረስ የማዳበሪያ ዝርፊያን ለመከላከል በእጀባ ስለሚጓጓዝ መዘግየት መኖሩን አንስተዋል። ስለዚህ ”ማዳበሪያ እንዳይዘገይ ሕዝቡ ለሰላሙ ከመንግሥት ጎን መቆም አለበት” ነው ያሉት።

ሌሎች የግብርና ሥራዎችንም ለማከናወን ሰላም አስፈላጊ ስለኾነ ሕዝቡ ለሰላም ቁርጠኛ ኾኖ እንዲቆም አሳስበዋል።ግብርናውን ለማዘመን እየተሠራ መኾኑንም ኀላፊው ገልጸዋል።

👉 የመካናይዜሽን ትግበራ እና የክላስተር አሠራር መጀመሩ፣
👉 የምርጥ ዘር አጠቃቀም ማደጉ፣
👉 የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ መጠናከሩ፣
👉 የሌማት ቱሩፋት መጀመሩ፣
👉 የኮንትራት ፋርሚንግ አመራረት መስፋፋቱ እና
👉 ስንዴን በበጋ ማምረት፣

ለውጥ ያመጡ የግብርናው ዘርፍ ዝመና መገለጫዎች መኾናቸውን ዶክተር ድረስ ሳህሉ አብርተዋል።

ሥነ ምህዳርን ማዕከል ያደረገ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት እየተሠራ መኾኑንን ኀላፊው ገልጸዋል። በቆጋ መስኖ ልማት ማንጎ ወደ ውጪ እስከመላክ መደረሱንም በዋቢነት አንስተዋል። ችግኝ ጣቢያዎች በየወረዳው ተቋቁመዋል። ለማንጎ በሽታ መፍትሄ እየተፈለገ ነው። አትክልቶችን በክላስተር የማልማት ሥራን እየተሠራ ነው ብለዋል።

ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት ትኩረት መሰጠቱን ነው ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የገለጹት። የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን መቋቋሙንም ጠቁመዋል። የምርጥ ዘርን እና የምርቶችን ጥራት ከንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ደረጃቸውን የጠበቁ እንደ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር ያሉ ምርቶች እንዲመረቱ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደሴ ከተማ አሥተዳደር የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ መርሐ ግብር በይፋ አስጀመረ።
Next article“ጥር 23 አይቀርም፤ እንጀባራም እንግዶቿን አዲናስ ብላ ለመቀበል ዝግጅቷን ጨርሳለች” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)