
ደሴ: ጥር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ የ2016 ዓ.ም የግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማውን በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) የሚቀርቡ የሥራ እድል ፈጠራ ሪፖርቶች መሬት ላይ ካለው ሐቅ ጋር የተመሳከሩ መኾን እንዳለባቸው አሳስበዋል። መሬት ላይ ካለው ሐቅ ጋር የሚቃረኑ የሐሰት ሪፖርቶችን ችግር ለመቅረፍ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የመረጃ አያያዝ ሊኖር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
“በክልሉ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ በየአካባቢው ያለውን ፀጋ የመለየት እና ወደ ጥቅም የማስገባት ሥራ እየተከናወነ ነው” ብለዋል ቢሮ ኀላፊው። የሥራ ተነሳሽነትን መፍጠር፤ ለሥራ ዝግጁ የኾኑ ወጣቶችን መደገፍ እንዲሁም ቴክኖሎጂን ማሸጋገር እንደሚገባም ዶክተር አሕመዲን ተናግረዋል።
በሥራ እድል ፈጠራ ላይ በግማሽ ዓመቱ የተስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ በቀሪ ወራቶች ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አወቀ ዘመነ በክልሉ በግማሽ ዓመቱ ከ600 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ቢታቀድም 181ሺህ ለሚኾኑት ብቻ ሥራ መፈጠሩን ገልጸዋል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መኾን ዋነኛ ምክንያት ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሀያት መኮነን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!