
ባሕርዳር: ጥር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ያለው ሰላም ከነበረበት የከፋ ግጭት በመውጣት በተሻለ ለውጥ ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ገልጿል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው የክልሉን ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ ደሳለኝ በመግለጫቸው እንዳነሱት አሁን ላይ ያለው የክልሉ የሰላም ኹኔታ በአንጻራዊነት የተሻለ ስለመኾኑ ገልጸዋል። በፊት ላይ የነበረው የከፋ የሰላም እጦት ችግር ተቀርፎ አሁን ላይ ማኅበረሰቡ አንጻራዊ ሰላም አግኝቷል፤ ወደ ልማትም እየተመለሰ ነው ብለዋል።
በጸጥታ ችግር እና በግጭት ምክንያት የተቋረጡ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች አሁን ላይ እየተካሄዱ ስለመኾኑም በመግለጫው ተጠቅሷል። ማኅበረሰቡ ሙሉ ጊዜውን ተጠቅሞ እና ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ለማልማት ያለውን ፍላጎት የሚያሟላ አስተማማኝ ሰላም በመገንባት በኩል ግን ገና ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ ነው የተናገሩት ቢሮ ኀላፊው።
ግጭቱ ከፈጠረው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግር ለመውጣት የሚያስችል አንጻራዊ ሰላም ለማስፈን ተችሏል፤ ዘላቂ እና ፍጹም ሰላምን በማስፈን ሕዝብን ለመካስ ደግሞ በቁርጠኝነት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ምንጩን በጥናት ለይተናል፤ እሱም ከራስ በላይ ለሕዝብ አለማሰብ የፈጠረው ችግር ነበር ሲሉም ተናግረዋል። አሁን ላይ ለጸጥታ አካላት አስፈላጊው ሥልጠና ተሰጥቷል፤ የሚናበብ እና ለሕዝብ ሰላም በሙሉ ጊዜ እና አቅም የሚሠራ ቁርጠኛ የጸጥታ ተቋም እና አባላትን የመፍጠር ሥራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
መንግሥት ለሰላም ሁሌም በሩ ክፍት ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ የተደረገው የሰላም ጥሪ ብዙ የተሳሳቱ አካላትን ዳግም እንዲያስቡ ያስቻለ እንደነበር ገልጸዋል።
በርካታ ወጣቶች በድርጊታቸው ተጸጽተው ወደ ሰላም በመግባት ሥልጠና ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ ተመልሰዋል ነው ያሉት። አብዛኛዎቹ ሕዝባቸውን በሚክስ የልማት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ እድል አግኝተዋል፤ ቀድሞውንም በጸጥታ አባልነት ሲያገለግሉ የነበሩት ደግሞ ወደመደበኛ ሥራቸው ተመልሰው የሕዝባቸውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ እገዛ እያደረጉ ስለመኾኑ በመግለጫው ተጠቁሟል።
አቶ ደሳለኝ የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለማረም ጠንካራ የጸጥታ ተቋም እንደሚያስፈልግ በመተማመን እየተሠራ ነው ብለዋል። ተጨማሪ የጸጥታ አካላት የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡም ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል።
በዚህ ሥልጠና ሕዝብን ከችግር አላቅቆ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለማሸጋገር የሚያስችል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዕውቀት እና ክሕሎት ለጸጥታ አባላት ይሰጣል ነው ያሉት።
“ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሕዝብ ተሳትፎ ወሳኝነት አለው” ያሉት አቶ ደሳለኝ ሕዝቡ በጨዋነት የሰላም ሥራው ተሳታፊ መኾን ይገባል ብለዋል።
በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከፍተኛ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ተፈጥሯ፤ አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሮ በመልሶ ግንባታ ሥራ ላይ ነን፤ ችግሩ ዳግም እንዳይፈጠር ሕዝቡ የበኩሉን ተሳትፎ ማድረግ አለበት ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!