
አዲስ አበባ: ጥር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ሕንፃ እና ዘመናዊ ስቱዲዮ እያስመረቀ ነው።
ኢዜአ እያስመረቀ ያለው ዘመናዊ የሚዲያ ሕንፃ ኮምፕሌክስ 3 የቴሌቪዥን እና 4 የራዲዮ ስቲዲዮዎች፣ ዘመናዊ የሚዲያ የቅንብር ቦታዎችን፣ ለቢሮ አገልግሎት የሚኾኑ በርካታ ክፍሎችን፣ የመሠብሠቢያ አዳራሾችን፣ ቤተ-መጻሕፍት፣ የመዝናኛ ማዕከል እና ዘመናዊ ጂምናዝየምን ያካተተ ነው።
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ኢዜአ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ ለማድረግ እዚህ በመድረሱ ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መረጃ እየሠበሠበ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ኢትዮጵያውያንን የመረጃ ባለቤት ሲያደርግ እንደቆየም አስገንዝበዋል።
ኢዜአ ከዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎች አንዱ እና ተወዳዳሪ የሚያደርገውን ሥራ እየሠራ ስለመኾኑም ነው ያስረዱት።
በቴክኖሎጅ ቀዳሚ ኾኖ ለመምጣት የሚያስችለውን አቅም መፍጠሩን ማየት በራሱ ኩራት እንደኾነ ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
ድርጅቱ በባለፈው 82 ዓመት የመጣበትን መንገድ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንደሚገባውም ነው ያሳሰቡት።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሚዲያ መሪዎችና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።
ከተመሠረተ 81 ዓመታትን የተሻገረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገጽታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ዘጋቢ:- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!