ተቋርጦ የነበረውን የተከዜ ዓሳ ሃብት ምርት ለማስጀመር መዘጋጀቱን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

26

ሰቆጣ: ጥር 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መንግሥት በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እየታየ ያለውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ ተቋርጦ የነበረውን የተከዜ ዓሳ ሃብት ምርት ለማስጀመር መዘጋጀቱን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

በአማራ ክልል እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት በዓሳ ሃብት አጀማመር እና የወደፊት አቅጣጫዎች ዙርያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሰቆጣ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።
ከስሃላ ሰየምት ወረዳ የመጡት አቶ ደሴ ዓለሙ ከጦርነቱ በፊት በዓሳ ማስገር ሥራ የተሻለ አቅም ፈጥረው እንደነበረ ተናግረዋል።

ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ሕገወጥ አስጋሪዎች በመበራከታቸው ሕጋዊ ማኅበራትን ሊያሠሩ እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡ መንግሥት አካባቢው ወደ ሰላም እንዲመለስ በማድረግ ሥራው እንዲጀመር ማድረጉ እንዳስደሰታቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ወጣት ካሣሁን ሙሉጌታ ዓሳ ተረካቢ ሲኾኑ የትራንስፖርት ችግር እና በሰላም እጦት ምክንያት የመብራት ኃይል ባለመኖሩ የዓሳ ምርቱ እንዲበላሽ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
በውይይት መድረኩ ማጠቃለያ ሃሳብ የሰጡት የዞኑ እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲሳይ አያሌው ዞኑ በዓሳ ሃብት ቀዳሚ ቢኾንም ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ከምርቱ ተጠቃሚ አልነበረም ብለዋል።

ሕገ ወጥ አስጋሪውን በማስቆም የተደራጁ ማኅበራት በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ጽሕፈት ቤቱ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የተፈጠረውን ሰላም በመጠቀም በሙሉ አቅም ዓሳን በማምረት ተጠቃሚ መኾን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ የመንገድ እና የመብራት ጥያቄዎቹም ከሰላሙ መረጋገጥ በኋላ በሂደት የሚፈቱ መኾኑንም አውስተዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ነገ ያስመርቃል።
Next article“የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከዓለም አቀፍ ዜና ወኪሎች ተወዳዳሪ የሚያደርገውን ሥራ እያከናወነ ነው” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)