የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ነገ ያስመርቃል።

28

ባሕር ዳር: ጥር 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በነገው እለት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ያስመርቃል።

የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎችም እንዳሉት ተገልጿል። ለቢሮ አገልግሎት የሚኾኑ በርካታ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ቤተ-መጽሐፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዝየም ያካተተ ነውም ተብሏል።

ከተመሠረተ 80 ዓመታትን የተሻገረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።

ለዚህም በመላው ሀገሪቱ 38 ቅርንጫፎችን በመክፈት በቅርቡ የጀመራቸውን ሶማሊኛ እና አፋርኛን ጨምሮ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋዎች አስተማማኝ የዜና ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።

በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም የኢትዮጵያን ገፅታና እውነታ ለዓለም ተደራሽ እያደረገ መኾኑም ነው የተገለጸው። ኢዜአ በ2022 በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት በላቀ ብቃት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ኢዜአ እንደዘገበው የስርጭትና ተደራሽነት አድማሱን በምስራቅ አፍሪካ ለማስፋት በኬንያና በጅቡቲ ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ ይገኛል። ኢዜአ በ1934 ዓ.ም በወቅቱ የጽሕፈት ሚኒስቴር ተብሎ ይጠራ በነበረው ተቋም፣ የጋዜጣ እና ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ስር እንደ አንድ የሥራ ክፍል መቋቋሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) የሚለውን መጠሪያና የዜና አገልግሎት ደረጃ ያገኘው በ1960 ዓ.ም በወጣው የመጀመሪያው የማቋቋሚያ አዋጅ ነው። በአዋጅ ቁጥር 1115/2011 በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ዋነኛ የዜና ምንጭ በመሆን ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠርና የሀገሪቱን ገጽታ የመገንባት ተልዕኮ ተሰጥቶታል።

ኢዜአ እስከ አሁን በመጣበት ረጅም የአገልግሎት ዘመን በሀገሪቱ በተመዘገቡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች ላይ የራሱን አሻራ እያሳረፈ ጉዞውን ቀጥሏል። አገልግሎቱ በአዲስ የከፍታ ምዕራፍ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ዜና እና ዜና ነክ ዘገባዎችንና ፕሮግራሞችን በፍጥነትና በጥራት ለሕዝብ ተደራሽ የሚያደርግ ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተማሪዎች የከተማው እና የዩኒቨርሲቲው ጌጦች በመኾናችሁ ሁሉም ማኅበረሰብ እንደ ልጅ ይንከባከባችኃል” የደባርቅ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች
Next articleተቋርጦ የነበረውን የተከዜ ዓሳ ሃብት ምርት ለማስጀመር መዘጋጀቱን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።