“ተማሪዎች የከተማው እና የዩኒቨርሲቲው ጌጦች በመኾናችሁ ሁሉም ማኅበረሰብ እንደ ልጅ ይንከባከባችኃል” የደባርቅ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች

20

ባሕር ዳር: ጥር 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ጥሪ ያደረገላቸው ነባር ተማሪዎች እየተቀበለ ነው። ተማሪዎች መግባታቸው ተከትሎ በዛሬው ዕለት ለተማሪዎች የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት እና በመማር ማስተማር አካሄድ ዙሪያ ገለጻ ተደርጓል፡፡ በዝግጅቱ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ተገኝተዋል።

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት እና የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት አስማማው ዘገዬ (ዶ.ር) ለረጅም ወራት የተቋረጠውን ትምህርት ለማስጀመር ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከተለያዩ አካላት ጋር ንግግር ተደርጓል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ከግብዓት እና ከሰላም አንፃር በቂ ዝግጅት ማድረጉንም አብራርተዋል፡፡

ተማሪዎችን በአግባቡ ለማስተናገድ እና የዘገየውን የመማር ማስተማር ጊዜ ለማካካስ ዩኒቨርሲቲው በቂ ዝግጅት እንዳከናወነም ተናግረዋል። ተማሪዎችም ሙሉ ጊዚያቸውን በጥናት እና በመማር ማስተማሩ እንዲያሳልፉ ዶክተር አስማማው አሳስበዋል።

የደባርቅ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አበባው አዛናው ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡በዝግጅቱ የተገኙ የሀገር ሽማግሌዎችም “ተማሪዎች የከተማው እና የዩኒቨርሲቲው ጌጦች በመኾናችሁ ሁሉም ማኅበረሰብ እንደ ልጅ ይንከባከባችኃል”ብለዋል፡፡

ተማሪዎችም ጥሪ ተደርጎ በመመለሳቸው መደሰታቸውን የተናገሩ ሲሆን የአካባቢው ኅብረተሰብ እና ተቋሙ ላደረገላቸው መልካም አቀባበል አመስግነዋል። ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንደሚያተኩሩ መግለጻቸውንም ከኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ድረ ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሐይቅ ከተማ ተገንብተው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች የሀገራችንን የለውጥ ጉዞ ውጤቶች ማሳያ ናቸው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next articleየኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ነገ ያስመርቃል።