
ደሴ: ጥር 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የሐይቅ ከተማ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ሰላማቸውን በመጠበቅ ልማትን ለማፋጠን እየሠሩ ያሉት ሥራ የሀገሪቱን እድገት እውን ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ አፈ ጉባኤዋ “በሐይቅ ከተማ ተገንብተው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች የሀገራችንን የለውጥ ጉዞ ውጤቶች ማሳያ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሀይቅ ከተማ ዙሪያ የሚገኘው ሎጎ ሐይቅ እና አካባቢው ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት እና ለልማቱም መፋጠን ትልቅ አቅም ያለው መኾኑንም ጠቁመዋል። የቱሪዝም ዘርፉ ለሀገር እድገት መፋጠን ጉልህ ድርሻ አለው ያሉት አፈ ጉባኤዋ ሎጎ ሐይቅን በማልማት ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እና ለአካባቢው ልማት መፋጠን በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በተሰማሩበት ዘርፍ ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ለሰላም መስፈን በትኩረት በመንቀሳቀስ እና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ አስተማማኝ ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋልም፤ በክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም አለው ሲሉም አፈ ጉባኤዋ አብራርተዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- አሊ ይመር
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!