
ደሴ: ጥር 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሐይቅ ከተማ አሥተዳደር በ77 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል። ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን እድገት ለማፋጠን ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ከድር መሐመድ ገልጸዋል።
ኢንቨስትመንትን በመሳብ የሐይቅ ከተማን እድገት ለማፋጠን እየተሠራ ነው ያሉት ከንቲባው በዓለም ባንክ፣ በክልሉ መንግሥት እና በከተማ አሥተዳደሩ በጀት በ41 ሚሊየን ብር ወጪ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሰሜኑ ጦርነት በርካታ መሠረተ ልማቶች ቢወድሙብንም የወደሙትን መጠገንን ጨምሮ የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ ተቋማትን በላቀ የጥራት ደረጃ መገንባት ችለናል ብለዋል። ዛሬ የተመረቁ ፕሮጀክቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን የሐይቅ ከተማን ጨምሮ የዞኑን እድገት ለማፋጠን የሚያግዙ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
“የሕዝብን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ሰላም ዋነኛ ሚና አለው” ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ልማትን ለማፋጠን ሕዝቡ ሰላሙን መጠበቅ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።
የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለመመረቅ የበቁት በዞኑ አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ ምክንያት መሆኑንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን “የተባበረ የሕዝብ እና የመንግሥት አቅም ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ ዋስትና ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ዛሬ የተመረቁት ግንባታዎች በአጭር ጊዜ መጠናቀቃቸው መንግሥት የፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተትን በማስቀረት የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመሥራት ላይ መሆኑን ማሳያ ናቸው ብለዋል። ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር የፕሮጀክት ሠራተኞችን የሥራ ተነሳሽነት መጨመር እንደሚገባም አመላክተዋል። ሠራተኞችም ቀልጣፋና ፍትሐዊ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዮችን እርካታ ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
የልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ በአካባቢው ያለው ሰላም አግዟል ብለዋል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ። በቀጣይም ሰላምን በማረጋገጥ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል። ለአካባቢው ልማት መፋጠን የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ:- አሊ ይመር
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!