
ባሕር ዳር: ጥር 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የኢትዮጵያ ሰላም አስጠብቃለሁ፣ ምንዳን ለልጆቻችን አወርሳለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር እና የደቡብ ጎንደር ዞን ሴቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
በመድረኩ የተገኙት ሴቶች የሰላም አምባሳደሮች እና ምሰሶዎች ነን ብለዋል። በመነጋገር እና በመወያየት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል። ሴቶች ስለ ሰላም ከሠሩ በአጭር ጊዜ የተሟላ ሰላም እንደሚመጣም ገልጸዋል። በዚህ ወቅት ከሰላም ውጭ የሚያሳስብ ነገር አለመኖሩንም ተናግረዋል።
ሴቶች ልጆቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን እና ባለቤታቸውን በመምከር ሰላም እንዲመጣ ማድረግ እንደሚችሉም ገልጸዋል።
በእውነት ላይ በመመሥረት ስለ ሰላም መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። በሰላም እጦት የተጎዳነው እኛው ነን፣ ለልጆቻችን ቆርሰን የምንሰጠው ያጣን ሰዎች አለን፣ ገበያ ሄደን የምንገዛው እያጣን እየተቸገርን ነውም ብለዋል። በአንድ ዓላማ በመጽናት ሰላምን ማምጣት ካልተቻለ የከፋ ችግር ውስጥ እንገባለን ነው ያሉት። በሰላም እጦት ምክንያት ሴቶች ወደ ሕክምና ተቋማት ሄደው ለመውለድ መቸገራቸውንም ገልጸዋል። የሰላም እጦቱ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ወገኖች ለከፋ ችግር እየተጋለጡ መሆናቸውንም አንስተዋል።
ለችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ ማፈላለግ መልመድ እንደሚገባም አመላክተዋል። በክልሉ የተፈጠረው የሰላም ችግር ያደረሰው ጉዳት ዘርፈ ብዙ መሆኑንም አንስተዋል። የትኛውም አካል እናቱን ከማስለቀስ ሰላምን መምረጥ ይገባዋልም ብለዋል። ስለ ሀገር ሰላም አንድ ሆኖ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። በርካታ ወገኖች ካለቁ በኋላ ሰላማዊ ውይይትን ከመምረጥ የከፋ ችግር ሳይመጣ በውይይት መፍታት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ቤተልሔም ክበቤ ሁሉም ሰው ስለ ሰላም መወያየት እና ስለ ሰላም መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። ችግሮችን በምክክር እና በንግግር መፍታት ይገባልም ብለዋል። በአንድነት ስለ ሰላም መስበክ እና ሰላምን ማፅናት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የደብረታቦር ከተማ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሞሚና አሊ የተፈጠረውን የሰላም ችግር መፍታት የሚቻለው በውይይት ነው ብለዋል። የሰላም እጦት ሴቶችን ቀዳሚ ተጎጅ እያደረጋቸው በመሆኑ ስለ ለሰላም መሥራት ግድ ይለናል ነው ያሉት። ወገኖቻችን ሲሞቱ ከማልቀስ ሞታቸውን የሚያስቀር ሥራ መሥራት አለብን ብለዋል። እርስ በእርስ በመጠፋፋት የሚመጣ ለውጥ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
የእናቶችን ሞት እና እንግልት ለመቅረፍ ችግሮችን በንግግር መፍታት ይገባል ነው ያሉት። ችግሮችን በሰላም የመፍታት እድል አሁንም መኖሩን ገልፀዋል። በሰላም እጦት ምክንያት የልጆችን እድሜ ያለ አግባብ ማሳለፍ እንደማይገባም ተናግረዋል። ሕዝብና መንግሥት በመግባባት እና በመደጋገፍ ሲሠሩ ሀገር እንደምትፀናም ገልጸዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ሴቶች ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ወንድሙ ሰላምን ለማምጣት የሴቶች ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። የችግሩ ምንጭ እና መፍትሔው ከእያንዳንዱ ቤት መኖሩንም ገልጸዋል። “በቆዬው ባሕል እና እሴት በመመካከር ችግሮችን መፍታት ይገባናል” ነው ያሉት። በሰላም እጦት የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ሰላምን ማስፈን ይገባል ብለዋል። ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሕዝብን ጥያቄዎች መፈታት እንደሚገባም አመላክተ