ሴቶች የክልሉ ሰላም እንዲረጋገጥ እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ።

13

ባሕር ዳር: ጥር 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የኢትዮጵያ ሰላም አስጠብቃለሁ፤ ምንዳን ለልጆቻችን አወርሳለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እና የደቡብ ጎንደር ዞን ሴቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ ነው።

በምክክር መድረኩ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ኀላፊ ወይዘሮ ቤተልሔም ክበቤ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ዜጎች ለችግር ተጋልጠዋል፤ የኑሮ ውድነት በእጅጉ አሻቅቧል ነው ያሉት። የጸጥታ ተቋማት ለሕዝብ ሰላም የከፈሉት ዋጋ ከፍተኛ መኾኑንም አመላክተዋል። በተሠራው ሥራ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ለሰላም እየገቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

ከሰላም ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። ሴቶች የክልሉ ሰላም እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ሴቶች አሁንም የአካባቢውን እና የክልሉን ሰላም ለማጽናት በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። ሰላማዊ እና በምጣኔ ሃብት የተሻለ አካባቢ እና ሀገር ለመመሥረት የሴቶች ሚና ላቅ ያለ መኾኑንም ገልጸዋል። የሰላም እጦት ሲኖር ቀዳሚ ተጠቂዎች ሴቶች መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም መጠበቅ፣ ማስጠበቅ፣ ማስከበር እና ማጠናከር ይገባናልም ብለዋል። ሀገራዊ አንድነትን በማረጋገጥ ሰላሟ የጸናች ሀገር ለማስከበር መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። በክልሉ በተፈጠረው ችግር ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል።

የሴቶች ጉዳት እንዳይቀጥል ሰላምን ማምጣት ይገባልም ብለዋል። በሰላም እጦት ምክንያት እናቶች ወደ ሕክምና ተቋማት ሄደው እንዳይወልዱ፣ ተማሪዎች ትምህርት ቤት እንደይሄዱ እና ሌሎች ችግሮች እንዲደርሱ ማድረጉን ነው የተናገሩት።

የተጀመረውን ሰላም ማጠናከር፤ ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል። ሴቶች የማኅበረሰብ መስተጋብር ምሰሶዎች መኾናቸውን የተናገሩት ኀላፊዋ ለኢትዮጵያዊነት ማኅበራዊ መስተጋብር ድርሻቸው ከፍ ያለ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሴቶችን ወደ መሪነት ማምጣት እንደሚገባም አመላክተዋል። አንድነት መዳኛ መንገድ መኾኑንም ተናግረዋል። መለያየት ዋጋ እያስከፈለ መምጣቱንም አስታውሰዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደበበ አክሎግ የአማራ ክልል በገጠው የሰላም መታወክ ችግር በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዋጋ ከፍለዋል ብለዋል። የደረሰው ችግር ባለበት ከቀጠለ የበለጠ እየከፋ ይሄዳል ነው ያሉት። በክልሉ በተሠራው የሕግ ማስከበር ሥራ አንፃራዊ ሰላም እየተገኘ መምጣቱንም ተናግረዋል።

ሴቶች የማኅበረሰብ መሠረት ናቸው ያሉት ኀላፊው ሰላምን ለማስፈን ያላቸው አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ነው ብለዋል። የሀገር ሰላም እንዲመጣ ያለባቸውን ኀላፊነት መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

በክልሉ ያለው የሰላም ችግር የሚቀረፈው እና ሰላም የሚረጋገጠው ሁሉም የድርሻውን ሲወጣ መኾኑንም አንስተዋል። የጥፋት መንገድ ይበቃናል ማለት ይገባናልም ብለዋል።

ሴቶች ለሰላም ዘብ በመኾን የአካባቢው ልማት እንዲቀጥል ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት። የሰላም ችግር ሁሉንም የሚጎዳ መሆኑን ያነሱት ኀላፊው ሁሉ ስለ ሰላም ዘብ መሆን እንደሚገባውም አንስተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወጣቱ ትውልድ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የሀገርን አንድነት ሊያስጠብቅ እንደሚገባ የሰቲት ሁመራ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
Next articleየአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በገበታ ለትውልድ የሚለማዉን ሎጎ ሐይቅ እየተመለከቱ ነው።