
ሁመራ: ጥር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሰቲት ሁመራ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት “እኔም ለሀገሬ የሰላም ዘብ ነኝ” በሚል መሪ መልዕክት ከከተማዋ ወጣቶች ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ውይይት አካሂዷል። በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ወጣቶች ተገኝተው የአካባቢን ሰላም ስማስጠበቅ እና ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ በሚኾኑባቸው መንገዶች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።
ወጣቶች የሀገር ኢኮኖሚ ልህቀትን የሚያስመዘግቡት፣ ዜጎች ተንቀሳቅሰው ንብረት የሚያፈሩት እና የሀገርን አንድነት ማስጠበቅ የሚችሉት የሰላምን አማራጭ ሲከተሉ መኾኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል። በተሳሳተ መረጃ ግጭትን አማራጭ ከማድረግ ይልቅ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የሥራ እድል በመፍጠር ወጣቶች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲኾኑ የከተማ አሥተዳደሩ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም በውይይቱ ላይ ተነስቷል። ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት እየሠሩ መኾኑም ተገልጿል። በየአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ተከታይ ረዳ ውይይቱ የከተማዋ ወጣቶች ለአካባቢያቸው ብሎም ለሀገር ሰላም ይበልጥ ዘብ እንዲቆሙ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የከተማዋ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ እያደረጉት ያለው ጥረት የሚደነቅ መኾኑንም ገልጸዋል።
ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን ፈለግ በመከተል ከሀሰተኛ መረጃዎች ራሱን በማራቅ ለሀገር ሰላም መኾን የበኩሉንን ኀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አቶ ተከታይ አሳስበዋል። የከተማዋን ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለ ድርሻና ከአጋር አካላት ጋር በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ዘጋቢ – ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!