
ባሕር ዳር: ጥር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በዘጠኝ ዞኖች በ45 ወረዳዎች በተከሰተ ድርቅ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጎች ለችግር መጋለጣቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋምም ከ16 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መሃሪ (ዶ.ር) የክልሉ መንግሥት ካለው በጀት ቀንሶ ግዢ በመፈጸም ምግብ ለማቅረብ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ችግሩ ሰፊ በመኾኑ እና በመንግሥት አቅም ብቻ ስለማይፈታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመንግሥታት እና የበይነ መንግሥታት የልማት አጋሮች እንዲያግዙ ጠይቀናል ብለዋል።
”የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ለዘላቂ ልማት እና የሕዝብ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል በተከሰተው ችግር ላይ ለመምከር በመንግሥት እና በአጋር አካላት የተዘጋጀ የአጋርነት፣ ትብብር እና የድጋፍ የውይይት መድረክም ተካሂዷል።
በውይይቱ በድርቁ ስፋት፣ የጉዳት መጠን፣ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲሁም መንግሥት እና የአጋር ድርጅቶች ምን እንደሚጠበቅባቸው ውይይት መደረጉን እና ግንዛቤ መያዙን ዶክተር ጥላሁን ተናግረዋል። አጋሮቻችን ባለፉት ጊዜያት ገጥሞን በነበረው ችግር እንዳደረጉት ሁሉ ይህንን የድርቅ ችግር ለመቋቋም እና ለመቅረፍም እገዛቸውን እንጠብቃለን ብለዋል።
የሆፕ ፎር ጀስቲስ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ደረጀ ዘለቀ በተከሰተው ድርቅ ሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች የበለጠ ለችግር ተጋላጭ መኾናቸውን እንደተረዱ ተናግረዋል። አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም ከአጋሮቻችን ጋር ተመካክረን እና ሃብት አፈላልገን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
የቀለም ኢትዮጵያ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ዳይሬክተር አብዱልአዚዝ አራጌ ድርጅታቸው በክልሉ ሲያደርጋቸው የነበሩ ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ሌሎች በጎ አድራጊ ድርጅቶችም የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። ራሱን አስችሎ ፕሮጀክት ነድፎ መሥራት፣ ከአሥተዳደራዊ በጀት ቀንሶ መጠቀም እና ከተጠባባቂ በጀት በመጠቀም ለተከሰተው ችግር ምላሽ መስጠት እንደሚቻልም ነው የተናገሩት።
የማኅበረ ሕይወት ፎር ሶሻል ዴቨሎፕመንት ዋና ዳይሬክተር ጥላየ ግዛቸው ድርጅታቸው ከ9 በላይ ፕሮጀክቶች እየተገበረ መኾኑን እና ለቀረበው ጥሪ ምላሽ ለመስጠትም ዝግጁ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይም ተጨማሪ ዕቅዶችን አዘጋጅተው ለጥሪው ምላሽ እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!