
ባሕር ዳር: ጥር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በሮም ጣልያን በተሰናዳ ክብረ በዓል የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸልመዋል። ሽልማቱ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በኾነው ከባቢያዊ ሁኔታ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ዕውቅና ለመስጠት የተበረከተ ነው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ ልዑካን ቡድኖች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ በጣልያን የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ተልዕኮዎች አባላት እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በተገኙበት ሽልማቱን ተቀብለዋል ።
ኢትዮጵያ ላለፉት አምስት ዓመታት በግብርናው መስክ ቁልፍ ኢንቨስትመንቶችን ያደረገች ሲኾን በስንዴ ምርት ራስን የመቻል ሥራዎችን በማከናወን በዐበይት ምርቶችም ላይ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግባለች።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!