“አጅባር የሠጋሮቹ መገናኛ፣ የጀግንነት መፈተኛ”

39

ባሕር ዳር: ጥር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እንደበኩር ልጅ እንክብካቤ የማይለያቸው፣ ባቄላ እና ገብስ የሚቆላላቸው፣ የጠራ ውኃ የሚቀዳላቸው፣ የተመቻቸ ማደሪያ የሚዘጋጅላቸው፣ ያማረ መዋቢያ የሚያሳምራቸው ያማሩ ፈረሶች እንደአሻቸው ይኾኑበታል፣ ከሜዳ ሜዳ እያካለሉ ሽምጥ ያዳርሱታል።

ልበ ሙሉነትን ከእናት አባቶቻቸው የወረሱ ጀግኖች፣ ሽንፈት ከሞት በላይ የሚመራቸው ኩሩዎች ከሁሉም ልቀው ለመገኘት ይፎካከሩበታል።

የፈረሳቸው ጌጥ፣ የፈረሳቸው ቁመና እና ወዘና አምሮ ይታይ ዘንድ ከፈረስ መርጠው ፈርስ ያሳድጋሉ፤ በጀግንነት ልቀው ይገኙ ዘንድ ፈረሶቻቸውን በለጋ እድሜያቸው ጀምሮ ቀጥተው ይገራሉ። ገብስ እና ባቄላ ለፈረሶቻቸው እያቀረቡ ይንከባከባሉ።

በሀገሬው በሜዳ የሚጋልቡበት፣ በዳገት የሚወጡበት ከፈረስም የተዋቡትን፣ ከበቅሎም ያማሩትን ማኖር የቆዬ ባሕል ነው። አባት ለልጅ እያወረሰ ሲወርድ ሲወራረድ ኖሯል። ያማረ ፈረስ መጋለብ፣ ያማረ በቅሎ መሸለም የክብርም መገለጫ ነው።

ፈረሶቻቸው እንደ ልጅ ይታዘዛሉ፤ እንደ ባለቤቶቻቸው ሁሉ መቀደምን እና መሸነፍን ሲጠሉ ያድጋሉ። ልቆ መገኘትን፣ ቀድሞ መድረስን፣ በጌታ ፊት መሞገስን እና መወደስን ይናፍቃሉ። አስቀድሞ ገና መሸለሚያው ሲደረብባቸው፣ ኮርቻው ሲቀመጥባቸው፣ እርካቡና ልጓሙ ሲስማማባቸው ወኔያቸው ይቀሰቀስባቸዋል። ሮጦ መቅደም፣ ቀድሞ መድረስ እና መወደስ ያምራቸዋል፣ እንደ ሰው ሁሉ ወኔ የሚሸነቁጣቸው ይመስካሉ። እርካቡ ተስማምቶ፣ ጌታው ከኮረቻቸው ላይ በኩራት ተቀምጦ በእግሩ መኮልኮል የጀመረ ጊዜ እግራቸውን አንስተው ይሠግራሉ። ፈረስ እና ጌታ ይስማማሉ፤ አብዝተውም ይግባባሉ።

በዚያች መለኮት በተገለጠበት፣ መንፈስ ቅዱስ በታየበት በታላቁ ተራራ ስሟን በወሰደች ከተማ አያሌ ታሪኮች፣ ዘመናትን የተሻገሩ ባሕሎች እና እሴቶች መልተዋል። አባት ያከበረውን ልጅም እያከበረው፣ አባት የገነባውን ልጅ እያጸናው እና እየጠበቀው ሕያው ምስክር የኾነ ታሪክ ታቅፋለች። እግር ጥሎት ለደረሰ ሁሉ ከሰፋው ታሪኳ እየጨለፈች፣ ከቆዬው ባሕሏ እየዘገነች፣ ከጸናው ሃይማኖቷ እየቀዳች ታስተምራለች። እንኳን የታሪክ ብራናዎቿ መረማመጃ ጎዳናዎቿ፣ በዙሪያ ገባዋ ያሉት ኮረብታዎቿ፣ መሠባሠቢያ ሜዳዎቿ ሁሉ ታሪክን ይነግራሉ፣ ባሕልን ያሳያሉ፣ ሃይማኖትን ያስተምራሉ ደብረታቦር።

ረዘም ያለ የምሥረታ ታሪክ ያላት ታሪካዊቷ ከተማ ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ እና ሊቃውንቱ ይቀመጡባት፣ ታሪክ ይሠሩባት፣ ጥበብን ያፈስሱባት፣ ራዕያቸውን እውን ያደርጉባት፣ ሕልማቸውን ይኖሩባት ዘንድ ሲመርጧት ኖረዋል። በዘመናቸው የከበረውን እና የተወደደውን ሁሉ አድርገውባታል። የስማቸው ማስታወሻ እና መሞገሻ የኾነ ታሪክም ጥለውባት አልፈዋል።

ሃይማኖት ይሰበክባታል፣ ሥርዓቱን ጠብቆ ይከበርባታል፣ ታሪክም ይነገርባታል፣ ባሕል ይገለጥባታል። በዚህች ከተማዋ ከሞሉት ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች መካከል አንደኛው አጅባር ሜዳ ነው።

በቀደመው ዘመን ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ ፣ መሳፍንቱ ፣ የጦር አበጋዞች፣ እንደ አንበሳ ግርማ ያላቸው ጦረኞች ተቀምጠውበታል፤ የጦር ስልት ነድፈውበታል። የነገሥታቱ ልጆች ልዑላኑ ፈረስ ጉግስ ተጫውተውበታል። ፈረሰኛ ጦረኞቹም በፈረሶቻቸው ሰግረውበታል፤ ከጦርነት በፊት የፈረሶቻቸውን ጉልበት እና ፍጥነት ለክተውበታል።

ሊቃውንቱም ሃይማኖትን አስተምረውበታል። ጉባኤያትን አድርገውበታል። እነሆ ዛሬም ድረስ ሊቃውንት ይሰባሰቡበታል፣ ሃይማኖትንም ያስተምሩበታል፣ ታቦታት ያድሩበታል፣ ዙሪያ ገባውን ይባርኩታል፣ ይቀድሱታል፣ የበዛ ሕዝብ ይሠባሠብበታል።

ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ በዓላትን ከእነ ሙሉ ሥርዓቱ እና ትውፊቱ ማክበር የምታውቀው ደብረታቦር በወርሐ ነሐሴ ደብረ ታቦርን በደብረታቦር እያለች በታላቅ ግርማ በዓሉን ታከብራለች። በወርሐ ጥር ደግሞ በዓለ መርቆሬዎስን በአጅባር ትደግሳለች። አጅባር በወርሐ ጥር ታቦታት ሳያድሩበት እና ሳይውሉበት የሚቀሩበት ቀናት ጥቂት ናቸው። ወርሐ ጥር በደረሰ ጊዜ ታቦታት ከመንበራቸው እየወጡ ወደ አጅባር ይወርዳሉ። በእልልታ እና በታላቅ አጀብ ታጅበውም ይደርሳሉ። በዚያም የተሠበሠበውን ሕዝብ ይባርካሉ።

ጥንታዊቷ ከተማ የምትደምቅበት፣ ጎዳናዎቿ የሚዋቡበት፣ ደጋጎቹ እንግዶችን ለመቀበል ሽርጉድ የሚሉበት፣ እልፍኞቻቸውን የሚያሳምሩበት፣ አዳራሾቻቸውን የሚያስጌጡበት፣ ጠላና ፍሩንዱሱን የሚያዘገጃጁበት በዓለ መርቆሬዎስ ቀርቧል።

በዓለ መርቆሬዎስ ደብረታቦር በደስታ ትመላለች። ከዳር ዳር በእልልታ ፣ በሆታና በዝማሬ ትመላለች። በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ታጌጣለች። ከጫጉላ የምትወጣ ሙሽራን ትመስላለች። ሙሽርነቷም ክብሯን እና ማንነቷን የጠበቀ ነው። በወይዛዝርቱ እና በጎበዛዝቱ ትከበባለች።

ለበዓለ መርቆሬዎስ የሚመረጠው ታሪካዊ ሜዳ አጅባር ይደምቃል። በሰውም ይጨነቃል። አበው አጅባርን ሜዳ ብቻ አይደለም ከሜዳ ያለፈ እንደቤተመቅደስ ነው ይሉታል። ለምን ቢሉ ታቦታት ያርፉበታል፤ ኪዳን ይደረስበታል፤ ቅዳሴ ይቀደስበታል፣ ስጋ እና ደሙ ይፈተትበታልና።

አጅባር ታሪክ የሚገለጥበት ብራናም ማነው አጅባር ባሕል የሚታይበት መስታወትም ነው፤ አጅባር ማንነት የሚገለጥበት ታላቅ ሥፍራ ነው። ጀግኖች ጀግንነታቸውን የሚያሳዩበት፣ ከሁሉም ልቀው ለመገኘት የሚፎካከሩበት የጀግንነት መግለጫም ነው።

በዓለ መርቆሬዎስ ቀርቧልና ደብረታቦር እንግዶቿን ትቀበል ዘንድ ተዘጋጅታለች። የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌትነት ከቤ ታሪካዊቷ ከተማ ለቱሪዝም የተመቹ ተፈጥሯዊ ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖትዊ ሥፍራዎች ያሉባት ናት ይሏታል። ደብረታቦር የበዙ የቱሪዝም ሀብቶች ያሉባት፣ ታሪክ ያከበራት ሥፍራም ናት። ከጥር 10 እስከ ጥር 29 ድረስ በከተማዋ ሃይማኖታዊ ሥርዓት በተከታታይ ይደረጉባታል፣ እኒህ በዓላት የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ናቸው ይሏቸዋል።

በከተማዋ መካከል ላይ የሚገኘው አጅባር ሜዳ ታሪክ እና ሃይማኖት የሚነገርበት ሥፍራ ነው። በዚህን ሥፍራ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትዕይንቶች ይካሄዱበታልና ለከተማዋ ውበትና ጌጥ ነው ። በዚህ ሥፍራ ታቦታት ሲወርዱ ሊቃውንቱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቀው ምሥጋና ያቀርባሉ፣ ፈረሰኞች በፈረስ ጉግስ ታቦታትን ያጅባሉ፣ ወይዛዝርቱ እና ጎበዛዝቱም እንደቀደመው ሁሉ ባሕሉን ጠብቀው በአጅባር ይገኛሉ። አጅባር የጸና ሃይማኖት እና ያልተበረዘ ማንነት የሚገለጥበት ነውና።

የቅዱስ መርቆሬዎስ የንግሥ በዓል እና የፈረስ ጉግስ ጨዋታ በከተማዋ ከሁሉም ልቆ ይከበራል ነው ያሉት። በዓለ መርቆሬዎስን በደብረታቦር ማክበር ልዩ ስሜት እና ትዝታ እንደሚሰጥም ነገረውናል። በአጅባር የሚካሄደው ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ድንቅ ያደርገዋል። በዓለ መርቆሬዎስ እንደ ቀደመው ሁሉ ተናፍቆ ይከበራል። በዓለ መርቆሬዎስን እና ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር የከተማዋ መገለጫ በማድረግ በልዩ ሁኔታ ለማክበር እየሠሩ መኾናቸውን ነው የነገሩን። ለበዓለ መርቆሪዎስ ክብረ በዓል ኮሚቴ ተቋቁሞ የዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነግረውናል።

አጅባር የሠጋሮቹ መገናኛ፣ የጀግንነት መፈተኛ ነው። ጀግኖቹ ፈረሶቻቸውን ሸልመው፣ ከየቀየው ተጠራርተው በአጅባር ሰማይ ሥር ይገናኛሉ። በዚያች ቀን አጅባር ከዳር ዳር ይሞላል።

በአጅባር ሰማይ ሥር የሚኾነውን ለማየት የሚጓጉ ሁሉ ምድር አልበቃ እያላቸው ዛፍ ላይ ወጥተው ትዕይንቱን ያደንቃሉ፤ ባዩት ነገር ይደነቃሉ፤ ይገረማሉ። የፈረሰኞቹ እልህና ትንቅንቅ አጀብ ያሰኛል። ሠጋር ፈረስና ጀግና ፈረሰኛ ይፎካከራል። የጀግንነት ልክ ይታያል። ምን ፈረስና ፈረሰኞቹ ብቻ በአጅባር ሰማይ ሥር የወይዛዝርቱ ጨዋታ፣ የጎበዛዝቱ ሆታ ሁሉም ልብን ይሠርቃል። የሊቃውንቱ ዝማሜ እና ምሥጋናም እጹብ ድንቅ ያሰኛል።

በበዓለ መርቆሬዎስ በአጅባር የተገኘ ሁሉ ሃይማኖትን፣ እሴትን፣ ባሕልን፣ ታሪክን፣ ማንነትን፣ ጀግንነትን እና አልሸነፍ ባይነትን በአንድ ላይ ያያል። ባየው ሁሉ ነፍሱ ሀሴትን ታገኛለች።

አጅባር ላይ ተሠባሠቡ በአንድ ጀንበር እልፍ ምስጢር ታገኛላችሁ። እልፍ ጥበብ ታደንቃላችሁ። ትናንት እና ዛሬን ትታዘባላችሁ። በድንቅ ማንነት፣ በውብ እሴት ትደመማላችሁ።

ከተማዋ ደብረታቦር፣ ሜዳው አጅባር ሥርዓቱ ድንቅ ነገር። አጅባር የታሪክ፣ የሃይማኖት የእሴት እና የማንነት ማሕደር።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ የባሕር በር የመፈለጓ መሰረታዊ መነሻ የህልውና ጉዳይ ነው” የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸለሙ።