“ኢትዮጵያ የባሕር በር የመፈለጓ መሰረታዊ መነሻ የህልውና ጉዳይ ነው” የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

28

ባሕር ዳር: ጥር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ለቀጣናው ሀገራት በሰላማዊ መርህ የቀረበ ህልውናን እና ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ መኾኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች ገለጹ።

የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ ማሕዲ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ እና የሕዝብ ቁጥር ያላት በመኾኗ አማራጭ ወደብ የግድ ያስፈልጋታል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማደግ፣ የወጪ እና ገቢ ንግድ መጨመርን ተከትሎ አንድ ወደብ ብቻ ኢኮኖሚዋን ሊሸከም አይችልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር የመፈለጓ መሰረታዊ መነሻ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው ከሶማሌላንድ ጋር ከተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ባሻገር ሌሎች ጥረቶችም ይቀጥላሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷ የግድ ቢሆንም የምትከተለው መርህ ሰላማዊ አማራጭ መሆኑን በመንግሥት ደረጃ መገለጹንም ነው ዶክተር ፈትሂ የተናገሩት።

የባሕር በር ጥያቄው ዋነኛ ግብ ኢትዮጵያ እና ጎረቤት ሀገራት ህልውናቸውን በትስስር የሚያረጋግጡበትን የነገ የአብሮነት ጉዞ የተለመ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አንድም ጊዜ ሌላ ሀገርን በኃይል ወርራ ወደብ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት የለም ያሉት ዶክተር ፈትሂ አቋሟ ሰላማዊ አማራጭ ብቻ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ባለው ባዬ በበኩላቸው አሁን በሀገሪቱ ያለው የሕዝብ ቁጥር፣ ቀጣናዊ ተለዋዋጭ ሁኔታ እና የኢኮኖሚ እድገት ያለ ወደብ ብዙ እርምጃ አያስኬድም ብለዋል።

መንግሥት አጀንዳውን ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ አድርጎ እንደያዘው እና የወደብ አማራጮችን ለማስፋት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

በቅርቡ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነትም የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በሕዝብ ቁጥርም በኢኮኖሚ እድገትም ቀዳሚ መሆኗን ገልጸው ከዚህ አኳያ እያደገ የመጣውን ፍላጎት በብቃት የሚሸከም ወደብ እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

የኮሚቴው አመራሮች ቀይ ባሕር የዓለም ንግድ ዋነኛ መተላለፊያ፣ የኃያላን የትኩረት ነጥብ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ካላት ቅርበት አንጻር ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በዝምታ አትቀመጥም ብለዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው ከወጪ ንግዷ ባሻገር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ አንገብጋቢ የሆኑ እንደ መድኃኒት፣ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ እና መሰል ምርቶችም የሚጓጓዙት በዚሁ መስመር በመሆኑ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ያሳስቧታል ነው ያሉት።

ቀጣናው ከዘጠኝ ያላነሱ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር ብዙ ሺህ ማይል ተጉዘው የጦር ሰፈር ሰርተው የሚንቀሳቀሱበት የመሆኑን ያህል አሸባሪዎች፣ ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች እና ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ንግድ የሚዘወተርበት መሆኑ ለኢትዮጵያ ስጋት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኢኮኖሚያዊ ህልውናዋን እና ሉዓላዊ ደህንነቷን ለማስከበር የባህር ኃይሏ የሚንቀሳቀስበት የባሕር በር እንዲሁም ለንግድ አማራጭ ወደብ የግድ እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምዕራብ ጎንደር እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞን አጎራባች ወረዳዎች የሚገኙ የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች በወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ እየመከሩ ነወ።
Next article“አጅባር የሠጋሮቹ መገናኛ፣ የጀግንነት መፈተኛ”