
ባሕር ዳር: ጥር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ስድስት ዓመታት በአማራ ክልል 19 ሺህ የባዮ ጋዝ ማብላያዎችን በመገንባት ከክልሎች ቀዳሚ በመኾን የአማራ ክልል ሀገር አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱን የክልሉ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ገልጿል።
በመላው ኢትዮጵያ ከተገነቡት ከ38 ሺህ በላይ የባዮ ጋዝ ማብላያዎች የአማራ ክልል ከ51 በመቶ በላይ ባለፈው ዓመት በሃገሪቱ ሊገነቡ ከታቀዱት ደግሞ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑትን በመገንባቱ ነው ዕውቅናው የተሰጠው።
ከክልሉ በተጨማሪም የደቡብ ወሎ ዞን በሀገሪቱ ከሚገኙ ክልሎች፣ በዞኑ የሚገኘው የወረኢሉ ወረዳ ደግሞ በሃገሪቱ ከሚገኙት ሁሉም ወረዳዎች የላቀ አፈጻጸም በማስመዝገብ ዕውቅና ማግኘታቸውን ገልጿል።
ከቢሮው ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው የበጀት ዓመት በአማራ ክልል ከ3 ሺህ 330 በላይ የባዮ ጋዝ ማብላያ በመገንባት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ቢሮው ባለፈው ዓመትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከታቀደው ከ60 በመቶ በላይ ማከናወን በመቻሉ ከተለያዩ አካላት ዕውቅና ሽልማት ተበርክቶለት ነበር። አሁን ቢሮው ያገኘው ሀገር አቀፍ የዕውቅና ሽልማትም የነዚህን ተከታታይ ውጤታማ ተግባራት ቀጣይነት በፌደራል ውኃና ኢነርጂ ሚኒስትልር፣ በብሔራዊ የባዮጋዝ ማስፋፊያ ፕሮግራም እንዲሁም በኔዘርላንዱ ግብረ ሰናይ ድርጅት SNV ማረጋገጥ በመቻሉ ነው ተብሏል።
የእውቅና ሽልማቱን የተቀበሉት የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊው ዶክተር ማማሩ አያሌው እንደተናገሩት የባዮ ጋዝ ማብላያ መገንባት ለኃይል አቅርቦት፣ ለግብርና ምርታማነትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት።
ይህንን በተግባር ለማዋል የሠራናቸው ተግባራት በሰላም እጦት በገበያ ዋጋ መዛነፍ ቢፈተኑም በየዓመቱ ከእቅዳችን በላይ መፈጸም ችለናል ነው ያሉት።
ለውጤቱ መሳካትም የአመራሩ የቢሮውና የተዋረድ መዋቅሩ ሠራተኞችንና የተጠቃሚውን ሕዝብ ተግባብቶ የመፈጸም ቅንጅት ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ቴክኖሎጂውን እንደተቀበለውም የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ቢሮው በክልሉ ለባዮ ጋዝ ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በ125 ወረዳዎች የግንባታ ሥራ እያከናወነ ነው።
ያለፈው ዓመት የቢሮው የዘርፉ አፈጻጸምም የእቅዱን 111 በመቶ በመፈጸም ያስቻለ ስኬት የተመዘገበበት መኾኑም ተገልጻል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!