
ባሕር ዳር: ጥር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ”የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ለዘላቂ ልማት እና የሕዝብ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ መልእክት በአማራ ክልል የተከሰተውን ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳትን ለመቀነስ በመንግሥት እና በአጋር አካላት የተዘጋጀ የአጋርነት፣ ትብብር እና የድጋፍ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በውይይቱ በክልሉ ከፍተኛ ድርቅ በመከሰቱ አሁን ላይ በ9 ዞኖች በ45 ወረዳዎች ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በድርቅ ምክንያት ለችግር መጋለጣቸው ተገልጿል፤ የቤት እንስሳትም የጉዳቱ ሰለባ ኾነዋል። የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍ የእለት ደራሽ ምግብ፣ ውኃ፣ ህክምና እና ሌሎች እርዳታዎች እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መሃሪ (ዶ.ር) ችግሮቹን ለማለፍ የክልሉ መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመንግሥት እና የበይነ መንግሥታት ድርጅቶችም አብረው እንዲሠሩ ለመነጋገር የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በድርቁ ምክንያት የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ የክልሉ መንግሥት ከመደበኛ በጀቱ ላይ በመመደብ እህል እያቀረበ መኾኑን ጠቅሰዋል። ይሁን እና በቂ ባለመኾኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም እንዲያግዙ ነው ዶክተር ጥላሁን የጠየቁት።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ እና ጦርነት ክልሉን ለችግር ተጋላጭ ማድረጉን ገልጸዋል። አሁን ላይ የተከሰተው የሰላም ችግር ተዘዋውሮ ለመሥራት ቢያስቸግርም ክልሉ 400 ሚሊዮን ብር በጅቶ እየሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ድርቁን የፈጠረውን ችግር በመስኖ ልማት ለመቀነስ የግብርና ልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን የገለጹት ዶክተር ድረስ በቀጣይም የድርቁን ችግር ሊያካክስ እና ሊመልስ የሚችል ሥራ መሠራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር ተባብረው የድርቅ ችግሩን ለመቅረፍ እንዲያግዙም ጠይቀዋል።
በክልሉ ከ170 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ይዘው በተለያዩ የልማት ሥራዎች እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!