
ባሕር ዳር: ጥር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ባሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች በርካታ ሀገራት ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ኢትዮጵያን በተለያዩ ሀገራት የወከሉ አምባሳደሮች ተናገሩ።
በተለያዩ የአለም ሀገራት ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮች በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
የልማት እንቅስቃሴዎቹም ለዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር አበርክቷቸው የላቀ መሆኑን አምባሳደሮቹ ተናግረዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አንዱ እና ዋነኛው ነው።
ይህን ለማሳካትም አምባሳደሮቹ በተመደቡባቸው ሀገራት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ትስስር ለመፍጠር እና ሀገራቱ ያላቸውን እምቅ አቅም ወደ ኢትዮጵያ እንዲያስገቡ እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ምርት እና ምርታማነትን የሚጨምሩ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ዋናው ጉዳይ መሆኑን ያስረዱት አምባሳደሩ ፓኪስታን በግብርና፣ በኬሚካል ኢንዱስትሪ፣ በማምረቻው እና በፋርማሲ ዘርፎች ትልቅ አቅም እንዳላት አስረድተዋል።
በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው የፓኪስታን አልሚዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን በማስታወስ የተጀመሩ ጥረቶች ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር በእጅጉ የሚያግዙ እንደሆነም አክለዋል።
ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጽኑ አቋም ያላት ሲሆን ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ 80 ባለሃብቶች መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
በብራሰልስ የቤሉክስ ሀገራት ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ በበኩላቸው በአውሮፓ ሀገራት ያሉ አልሚዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው አንስተዋል።
ለዚህም በሀገሪቱ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስተዋወቅ እና ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል የነበሩትን ጨምሮ በአዳዲስ ዘርፎች የሚሰማሩ አልሚዎች ከዚህ ወር ጀምሮ በስፋት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ አምባሳደር ሻሜቦ አክለዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ በበኩላቸው ጃፓን በቴክኖሎጂ ውጤቶች የተሻለ አቅም ስላላት በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግር ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያላትን የግብርና፣ የማዕድን እና ኢነርጂ ሃብቶች በማስተዋወቅ የጃፓን ባለሀብቶች መጥተው እንዲያለሙ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!