
ባሕር ዳር: ጥር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሚዲያዎች በመንግሥት አሰራር ውስጥ ግድፈቶች እንዲታረሙ የማሳየት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የማገዝ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ አሳስበዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያስገነባውን የፋና ላምሮት ስቱዲዮ እያስመረቀ ሲሆን በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ ቦርድ መሪዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ መገናኛ ብዙኃን በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ማኖር እንዲችሉ ሁነቶችን ከመዘገብ አልፈው ትኩረታቸውን በአሰባሳቢ ትርክት እና በትውልድ ግንባታ ሥራ ላይ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ባለብዝኀ መልክ በሆነችው ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ከሀገራቸውም ኾነ እርስ በእርስ የሚያስተዋውቁ ይዘቶች ላይ በማተኮር የሥነ ልቦና መቀራረብ መፍጠር እንዲሁም አብሮነትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር የሚዲያዎች ዋና ትኩረት መኾን እንዳለበት ተናግረዋል።
ሚዲያዎች እርስ በእርሳቸውም ሆነ ከሲቪል ማኅበራት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመሥራት በሀገር ግንባታ ላይ ያላቸውን ድርሻ በሚገባ መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉም ጠቁመዋል።
በተለይም በተልዕኮ፣ በይዘት እና በአሰራር ተቀራራቢ የሆኑ ሚዲያዎች ተገቢነት ከሌለው ፉክክር ወጥተው ትብብርን፣ ተቀራርቦ ተሞክሮ መለዋወጥን በማዳበር እና ለበለጠ ውጤታማነት ሰብሰብ ብለው በመቀናጀት የሀገሪቱን ገጽታ በተሻለ መልኩ መገንባት አለባቸው ብለዋል።
ስቱዲዮው በዋናነት የመዝናኛ ፕሮግራሞችን እና አሳታፊ መድረኮችን እንዲያስተናግድ ታስቦ የተገነባ ነው መባሉን ከብልጽግና ፓርቲ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!