
ባሕር ዳር፡ ጥር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የማዳበሪያ አቅርቦት ቀድሞ መድረስ መጀመሩ ለምርት እድገታቸው ወሳኝ እንደኾነ በደቡብ ጎንደር ዞን የጉና በጌምድር አርሶ አደሮች ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት የታየውን የማዳበሪያ አቅርቦት እና በማዳበሪያ አቅርቦቱ መዘግየት ምክንያት የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የአማራ ክልል ግብር ቢሮ በፌዴራል መንግሥት የተፈቀደለትን ማዳበሪያ ወደ ክልሉ አስቀድሞ ማጓጓዝ መጀመሩንም አሚኮ መዘገቡ ይታወሳል። አስቀድሞ መኋጓዝ የጀመረው ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየደረሰም ነው። በደቡብ ጎንደር ዞን የጉና በጌምድር ወረዳ አርሶ አደሮችም ማዳበሪያው አስቀድሞ መድረሱ ተስፋ ሰጪ መኾኑን ተናግረዋል።
ማዳበሪያ ሲወስዱ ያገኘናቸው አቶ አምባቸው ካሰው ወቅቱ ድንች የሚዘሩበት መኾኑን ገልጸዋል። ድንች ለማልማት የማዳበሪያ እጥረት ይገጥማቸው እንደነበር አስታውሰዋል። አካባቢው የግብዓት አቅርቦት በሰፊው እንደሚፈልግም ተናግረዋል። መሬታቸውን ደጋግመው አርሰው ለልማት ማዘጋጀታቸውንም ነው የሚናገሩት። ዘንድሮ የማደባሪያ አቅርቦት ቀደም ብሎ መድረሱንም ተናግረዋል። የማዳበሪያ ዋጋው ከባለፈው ዓመት አንፃር ቅናሽ እንዳሳየም ተናግረዋል። እየቀረበ ስላለው ማዳበሪያም አመሥግነዋል።
ሰላም ሲኖር የምንጠይቀው ይመጣል፣ ፍላጎታችን ይመለሳል ያሉት አቶ አምባቸው ፤ ሰላም በመታየቱ ማዳበሪያ ደርሶልናል ነው ያሉት። “ልጆቻችንን እና ወንድሞቻችንን እንመክራለን፣ ሀገራችን ሰላም እንድትኾን እንፈልጋለን” ብለዋል። ሰላም ከሌለ መኖር የለም፣ መኖር ያለው በሰላም ነው ብለዋል።
ሌላኛው ማዳበሪያ ሲወስዱ ያገኘናቸው ተስፋዬ ምሕረት ለስንዴ እና ለገብስ ዘር መሬታቸውን እያለሰለሱ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ባለፈው የምርት ዘመን የማዳበሪያ ችግር ቅሬታ ፈጥሮባቸው እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ የማዳበሪያ አቅርቦት ቀድሞ በመድረሱ መደሰታቸውንም ተናግረዋል። የሰላሙ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱንም ገልጸዋል። የማዳበሪያ አቅርቦት በተጨማሪ እንዲቀርብላቸውም ጠይቀዋል። አቶ ተስፋዬ ከማረስ እና ከማፈስ በተጨማሪ ሰላም እንዲኖር የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
ማዳበሪያ ሲወስዱ ያገኘናቸው ለማ ባንቴ መሬታቸውን አለስልሰው ሲጠብቁ እንደነበር ነው የገለጹት። አቶ ለማ ቀደም ብሎ ማዳበሪያ መምጣቱ የሚያሥመሠግን መኾኑን ነው የተናገሩት። ከአሁን ቀደም በማዳበሪያ እጥረት የዘር ወቅት ያልፋቸው እንደነበር የተናገሩት አቶ ለማ ዘንድሮ ቀድሞ በመምጣቱ በወቅቱ መዝራት እንደሚያስችላቸውም ተናግረዋል። ሰላም የሚያናጋ እንዳይኖር ቤተክርስቲያን ላይ አውግዘው ስለ ሰላም እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የጉና በጌምድር ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ካሴ አምባቸው በወረዳው ከ18ሺህ ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት መኖሩን ተናግረዋል። ከ37 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ወረዳው ለማስገባት አቅደው እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በተገኘው አንፃራዊ ሰላም ማዳበሪያ በመቅረብ ላይ ነው ብለዋል።
ማዳበሪያ መግባት የጀመረበት ወቅት ቀድሞ መሆኑንም አመላክተዋል። አሁን በተጀመረበት ልክ ከቀጠለ በአጭር ጊዜ እቅዳቸውን እንደሚያሳኩም ገልጸዋል። ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ላይ የተሻለ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። የግብርና መሪዎች እና ባለሙያዎች ከአርሶ አደሮች ጋር ለመገናኘት ሰላም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የተጀመረው ሰላም ዘላቂ ሊኾን ይገባልም ብለዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አባተ ሽባባው በዞኑ 560 ሺህ ሄክታር መሬት ለማረስ እቅድ መያዙን ገልጸዋል። 975 ሺህ 513 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ከ59 ሺህ በላይ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ዞኑ ደርሶ ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ መኾኑንም አመላክተዋል። የአፈር ማዳበሪያው ያለምንም ችግር ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ ኮማንድ ፖስቱ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። የአፈር ማዳበሪያ ቀድሞ መድረስ በመጀመሩ የነበሩ ችግሮች ሊኖሩ እንደማይችሉም አመላክተዋል። ለመስኖ ልማት በቂ ማዳበሪያ መኖሩንም አስረድተዋል። የሚገባው ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በአፋጣኝ እንዲዳረስ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!