
አዲስ አበባ: ጥር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለሁለት ሳምንት ሲካሄድ የነበረዉ የአምባሳደሮች ዓመታዊ ስብሰባ ተጠናቋል። በማጠቃለያ መድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተገኝተው ለሚሲዮን መሪዎች የሥራ አቅጣጫ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዓቀባይ አምባሳደር ዶክተር መለሰ ዓለም ገልጸዋል።
እንደ ቃል አቀባዩ ገለፃ አምባሳደሮች በሁለት ሳምንት ቆይታቸው በኢትዮጵያ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል። በተጨማሪ የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን፣ መከባበርን እና ሽርክናን መሠረት አድርጎ መቀጠል እንዳለበት እና የሚሲዮን መሪዎች አበክረዉ ሊሠሩ እንደሚገባ አቶ ደመቀ መኮንን አቅጣጫ መሰጠታቸውንም ቃለ ዓቀባዩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲያ እንዲጎለብትም አምባሳደሮች የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ እንዲገነቡ እና የውጭ ባለሀብቶች ኢትዮጵያን ምርጫ እንዲያድረጉ መሥራት እንዳለባቸው ተገልጿል።
ዘጋቢ:- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!