
ሰቆጣ፡ ጥር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ያስገነባውን ዘመናዊ ባለ ሦስት ወለል ሕንጻ አስመርቋል። የምክር ቤት ሕንጻውን መርቀው ያስጀመሩት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ ሕንጻው ለብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤቱ ብቻ ሳይኾን ለሌሎች ተቋማትም የሚሰጠው ፋይዳ የጎላ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ለሁሉም ቢሮ ግብዓት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ለመደገፍ አሥተዳደር ምክር ቤቱ ዝግጁ እንደኾነ አስረድተዋል።
ደረጃውን የጠበቀ ሕንጻ ተገንብቶ በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ለምክር ቤት አባላቱ ገልጸዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ በ2010 ዓ.ም የሕንጻ ሥራው እንደተጀመረ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በጦርነቱ እና በዲዛይን ችግር ምክንያት በሰዓቱ መጠናቀቅ እንዳልቻለ ነው ያብራሩት።
ዛሬ ለአገልግሎት የበቃው ዘመናዊ ባለ ሦስት ወለል ሕንጻ አጠቃላይ ወጭ 26 ሚሊዮን ብር በላይ መኾኑንም ገልጸዋል።
አፈ ጉባኤዋ ባቀረቡት ሪፖርት ሕንጻው የቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች፣ ሦስት የመሠብሠቢያ አዳራሽ ፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የባሕል ሙዚየም፣ ዘመናዊ የካፍቴሪያ እና የሱቅ ክፍሎችን ያካተተ መኾኑን ተናግረዋል። በቀጣይም ሕንጻው ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የቢሮ ቁሳቁስ ወጭ የሚጠይቅ በመኾኑ አሥተዳደር ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ያስገነዘቡት።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!