
አዲስ አበባ፡ ጥር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ዓድዋን ለዘላቂ ሰላም እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው።
የሰላም ሚኒስቴር ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ የተገኙት በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ.ር) ወጣቱ ትውልድ የሚሻትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ተመልካች ሳይኾን ከፍተኛ ሚና የሚወጣ መኾን ይገባዋል ብለዋል።
አድዋ በጋራ የመቆም ተምሳሌት ነው ያሉት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኑራ አህመድ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የማይገልጡ በርካታ ችግሮችን በማስወገድ የአድዋን የኅብረት እና የአንድነት ኀይል እሴትን ማዳበር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ይህ የወጣቶች ንቅናቄ የውይይት መድረኮች እስከ አድዋ ድል ቀን መዳረሻ በቀጣዩ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይደረጋሉ ተብሏል።
በእነዚህ የወጣቶች ውይይት መድረኮችም ሀገራዊ እሴት፣ ማንነት እና ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ምክክር ይደረጋልም ተብሏል።
ዘጋቢ፦ እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!