
ባሕር ዳር: ጥር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን ካላቸው ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶች መካከል ግጭትን የሚፈቱበት የእርቅ ሥነ ሥርዓት አንዱ ነው።
በአማራ ክልልም ግጭትን አስወግዶ በሰላም ለመኖር ሽምግልና እና እርቅ የተለመዱ የግጭት መፍቻ መፍትሄዎች ናቸው። በየአካባቢው ከሚታወቁት መካከልም የሀገር ሽማግሌ፣ የነፍስ አባት፣ ደም አድርቅ፣ ዘወልድ፣ አበጋር እና የፈረሰኞች ማኅበር ተጠቃሾች ናቸው። አለቃ ጥላየ አየነው በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የአገው ፈረሰኞች ማኅበር አለቃ ናቸው። ማኅበራቸው በየዓመቱ ከሚያከብረው የፈረስ በዓል ጀርባ ማኅበረሰቡ በመተሳሰብ፣ በመቻቻል እና በሰላም እንዲኖር ይሠራል። ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ ሲወርር ፈረሰኛ ከእግረኛ ሆ! ብሎ ጦሩን ስሎ ዘገሩን ወድሮ የተመመው የአገው ሕዝብ ዛሬ በአማን ጊዜ ፈረሱን ለእርቅ እና ለሰላም እየተጠቀመበት ነው።
ከጦር አውድማ ድል የተመለሱት የአገው ፈረሰኞች ከ84 ዓመት በፊት ‘አይነጥለን አይጎንጥለን’ ብለው ያቋቋሙት ማኅበር ለምቶ እና ሰፍቶ ሀገር ኾኗል። ለነጻነት ተጋድሎ ሽምጥ የጋለበውን ፈረስ ዛሬ ለሰላም፣ ለመቻቻል እና ለዘላቂ አንድነት እያሰገረው ነው። ባለ 64 ሺህ 221 አባሉ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር 6 ሺህ 500 አለቃ እና አጋፋሪዎች አሉት። የተጣላ ያስታርቃል፣ የተቀማ ያስመልሳል፣ እናም የማኅበረሰቡን የሰላም ችግሮች በመፍታት በኩል ሁነኛ ተቋም ኾኗል። ”ተበደልኩ ያለ ሰው ከፖሊስም ከፍርድ ቤትም በፊት በየደረጃው ለሚገኝ የማኅበሩ አስታራቂ ኮሚቴዎች ነው የሚያመለክተው” ይላሉ አለቃ ጥላየ።
”ሰብል ስናጭድም ስንወቃም ሁሉንም ሥራዎች በጋራ የመሥራት ባሕል አለን” ያሉት አለቃ በማኅበሩ የታቀፈ ሰው በሁሉም ሥራ እንደሚታገዝ አመላክተዋል። አንድ ሰው በጋራ የሚሠራ ሰርግ፣ ዝክር ወይም ሌላ ሥራ ሲኖረው የተቀያየመውን ሰው ቀድሞ ይታረቃል። በተለይ ለግብዣ የሚጠራ ሲኾን የተኳረፈውን ሰው አስታርቁኝ እንደሚል ነው አለቃ ጥላየ የገለጹት።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሁሉም ቀበሌዎች የፈረሰኞች ማኅበር እና የአስታራቂ ኮሚቴዎች መኖራቸውን የገለጹት አለቃ ጥላየ ማኅበሩ በችግር እና በደስታ ጊዜ ተባብሮ ለመኖር፣ ለፍቅር እና ለሰላም አግዞናል ይላሉ። ሥራዎችንም በጋራ ለመሥራት እየጠቀመን ነው’ ብለዋል።
ወደ ፖሊስ እና ፍርድ ቤት ከመሄድ ይልቅ በማኅበሩ መዳኘት የተለመደ ኾኗል። በማኅበሩ የተዳኙ ሰዎች ሁለቱም አሸናፊ እና ተሸናፊ ሳይኾኑ አትራፊ ናቸው ሲሉም ጠቀሜታውን ገልጸዋል። በማኅበረሰቡ ባሕል እና በማኅበሩ አሠራር መሠረት በግጭት የቀረቡ ሰዎችን መክሮ የተቀማን አስመልሶ የተበደለን አስክሶ ይቅር አባብሎ በወንድማማችነት ያስታርቃል። በመኾኑም ኅብረተሰቡ በመንግሥታዊ ተቋማት ከሚፈረድበት እና ከሚፈረድለት የተሻለ ማኀበራዊ መረጋጋትን እየፈጠረለት እንደኾነ ነው ያብራሩት።ይህ የማስታረቅ ልምድ የፖሊስ እና ፍትህ ተቋማት የሥራ ጫናን እንዳቃለላቸው ነው የገለጹት። “በማኅበሬ ልጠየቅ” እስከማለት የደረሰ ልምድም እየዳበረ ነው። ፖሊስ እና ፍትሕ የኛን ማኅበር በማጠናከር ለአካባቢው ሰላም ይጠቀምበታል ብለዋል አለቃ።
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር ሙሉሰው ታሪኩ የግጭት አፈታት ባሕላዊ እሴቶቻችን ከጥንትም ማኅበረሰብን ሲያገለግሉ የነበሩ ለአሁኑ ትውልድም የሚያገለግሉ መኾናቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያውያን ባሕል እና ታሪክ መተሳሰብ፣ መረዳዳት እና በጋራ መኖር መኾኑን የጠቀሱት ምሁሩ ሌሎች ሀገራት ወደገቡበት የግለኝነት አዘቅት ጨርሰን እንዳንገባ ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶቻችን ማኅበረሰቡን አጋምደው በመያዝ እያገለገሉ ናቸው ብለዋል።
የእርቅ ሥርዓቱ ‘ያሸነፈ ይኖራል’ እና ‘የአንዱ ህልውና ቀጣይነት የሚረጋገጠው ሌላውን በማጥፋት ነው’ የሚሉትን የምዕራባውያን የግለኝነት መርህ እና ጫናን ኢትዮጵያውያን በመተሳሰብ እና በመተዛዘን እሴቶቻቸው ተቋቁመው ሰላምን ለማስፈን ትልቅ ሚና እንደሚጫዎቱ ነው መምህሩ ያብራሩት።
ባሕላዊ የሽምግልና እና እርቅ እሴቶቻችን መዳከም ቢታይባቸውም ጨርሰው አለመጥፋታቸውን መምህር ሙሉሰው ጠቅሰዋል። ቢጠናከሩ ተቻችሎ በሰላም ለመኖር ያላቸው ዋጋ ተኪ እንደሌለውም ገልጸዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ለይኩን ሲሳይ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር አባላቱ ያልኾኑትን ጭምር በማስታረቅ ሰፊ ልምድ እና አቅም እንዳለው ገልጸዋል። ማኅበሩ በመደራጀቱ ብቻ ሳይኾን አባት ያቆየው በመኾኑ ፈረስ ያለውም የሌለውም አባል መኾን ይችላል። የጸጥታ ኃይሎችም በአብዛኛው ችግሮችን የሚፈቱት በፈረሰኞች ማኅበር በኩል መኾኑን ገልጸዋል።
የእርቅ ባሕሉ ለሰላም ችግሮች አፈታትም ትልቅ አቅም እየኾነ ነው ያሉት አቶ ለይኩን በውጤቱም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግጭቶች የከፉ አለመኾናቸውን ገልጸዋል። ”በአካባቢያችን ተፈጥሮ የነበረን ግጭት እና መፈናቀል በተከሰተ በ15 ቀን ውስጥ በሽምግልና ተፈትቶ ወደነበረበት መመለስ ችለናል” ብለዋል።
በመተሳሰብ፣ በመቻቻል እና ይቅር በመባባል ችግሮችን እየፈታ በአብሮነት ለዘለቀው የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ትልቁን ሚና እየተጫወተ ነው። በሌሎች አካባቢዎችም ባሕላዊ ተቋሞችን በማጠናከር ሰላምን በእጅ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የመከሩት። ሁሉን ነገር ወደ መንግሥት ተቋማት ብቻ ከመውሰድ ችግር ፈቺ እና ማኅበራዊ ቅቡልነት ያላቸውን ቀደምት የሽምግልና ሥርዓቶች በማጠናከር ሰላምን ማስፈን እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!