ለፖሊሲ ቀረፃ እና ማሻሻያ እንዲሁም ለልማት ተግባራት አጋዥ ነው የተባለትን ጥናት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ይፋ አደረገ፡፡

15

ባሕር ዳር: ጥር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እና ዓለም ባንክ በጋራ ያጠኑት ይህ ጥናት የኢትዮጵያ ሶሺዮ-ኢኮኖሚ ጉዳይን ያካተተ እንደኾነ ተገልጿል።

ጥናቱ ለመንግሥት የፖሊሲ ቀረፃ እና ማሻሻያ እንዲሁም ለልማት ተግባራት አጋዥ የሚኾኑ ሀገራዊ እና ማኅበረሰባዊ ሁነቶችን ዳስሷል ተብሏል።
ጥናቱ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነው የቀረበው፡፡

በጥናቱም በግብርናው ዘርፍ በአውሮፓውያኑ ዘመን በ2019 ላይ ምርጥ ዘር ይጠቀሙ ከነበሩት 38 በመቶ አርሶ አደሮች በ2022 ወደ 43 በመቶ አድጓል ተብሏል።
በአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ በተሠራው ጥናትም ከሦስት ሁለት እጁ አርሶ አደር ተፈጥሯዊ ያልኾነ የአፈር ማዳበሪያን ይጠቀማል ተብሏል።

ዜጎች በተለይም በ2022 ላይ በስፋት የሚያነሷቸው ችግሮች 2019 ላይ ያነሷቸው ከነበሩት እጅጉን የሰፉ መኾናቸው በጥናቱ ተመልክቷል።
በ2019 በምግብ ግብዓቶች ላይ በሚደረግ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት ይጎዳ የነበረው 5 በመቶ ማኅበረሰብ በ2022 ወደ 29 በመቶ አድጓል ነው የተባለው።

በ2019 የውኃ አገልግሎት ያገኝ የነበረ ማኅረሰብ 58 ሚሊዮን ወይም 70 በመቶ የነበረ ሲኾን በ2023 የውኃ አገልግሎት የሚያገኘው 73 ሚሊዮን ወይንም 74 በመቶ መድረሱን ጥናቱ አመልክቷል።

የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ ከ50 በመቶ ወደ 63 በመቶ አድጓል። ለዚህ ደግሞ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት አጋዥ ነበር ተብሏል።
በትምህርት ዘርፍ ላይ በተደረገው ጥናትም በ2019 እና በ2022 ላይ ተቀራራቢ ሂደት ላይ ያለ መኾኑን ጥናቱ አመላክቷል። 66 በመቶ ሴቶች 63 በመቶ ወንዶች በትምህርት ገበታ ላይ ናቸውም ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲካል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ.ር) ጥናቱ ለመንግሥት ፖሊሲ ጥናት እና ማሻሻያ እንዲሁም ለልማት ተግባራት ተደራሽነት አጋዥ ነው ብለዋል።
ይህ ከዓለም ባንክ ጋር ለ5ኛ ዙር የተደረገው ጥናትም በተሻለ ቴክኖሎጂ እና የናሙና ሥራ የተከናወነ ቢኾንም የጸጥታ ችግሮች ግን እጅጉን ፈታኝ እንዳደረጉበት አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ተመስገን ጥሩነህ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን በአብላጫ ድምጽ ተመረጡ።
Next articleየብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መግለጫ አውጥቷል።