ባሕርዳር ከተማ ከንግድ ባንክ ተጠባቂው የፕሪሜየር ሊግ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።

24

በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።ባሕርዳር ከተማ ከንግድ ባንክ 9 ሰዓት፣አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ደግሞ 12 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።
አምና የፕሪሜየር ሊጉ ድምቀት የነበሩት የጣናሞገዶቹ አጀማመራቸው የተሻለ ስለነበር በዓምና ጥንካሪያቸው ናቸው ለማለት ያስደፍር ነበር።

ነገር ግን ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ አለማግኘታቸው ቡድኑ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል።

በቀላሉ አሸናፊ ይሆንባቸዋል ተብሎ በተገመቱባቸው ጨዋታዎች ነጥብ መጣሉ ደግሞ ከፕሪሜየር ሊጉ መሪ ስምንት ነጥብ እንዲያንስ አድርጎታል።ቡድኑ በ19 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በዛሬው ጨዋታ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ያሬድ ባየህ በቅጣት ቡድኑን አለማገልገሉ ለደግ አረገው ቡድን ክፍተት እንዳይፈጥር አድርጓል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፕሪሜየር ሊጉ ክስተት ኾኖ ቀጥሏል።እስካሁን የገጠመው አንድ ሽንፈት ብቻ መኾኑ የጥንካሬው ማሳያ ነው።

በደረጃ ሰንጠረዡም በመቻል በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ ሁለተኛ ላይ ይገኛል።ዛሬ ነጥብ ማሳካት ከቻለም ወደ መሪነት ይመጣል።
ሁለቱ ቡድኖች በታሪክ የሚገናኙት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።ጨዋታው ቀን 9ሰዓት የጀምራል።

ምሽት 12 ሰዓት ደግሞ አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ይጫወታሉ።አዳማ ከተማ ጨዋታዎችን በሜዳው እያካሄደ ቢኾንም ውጤቱ ግን ብዙ የሚኮራበት አይደለም።
ቡድኑ ሙሉ ሦስት ነጥብ ካሳካ አምስት ጨዋታዎች ተቆጥረዋል።በሊጉ ዘጠነኛ ደረጃ ላይም ተቀምጧል።

ሀዋሳዎችም ከአዳማ ጋር የተቀራረበ ጉዞ ላይ ናቸው።በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደው በመጨረሻ ጨዋታቸው ወደ ድል ተመልሰዋል።
አሁን ላይ በደረጃ ሰንጠረዡ 11ኛ ደረጃን ይዘዋል።

በአስማማው አማረ

Previous articleበዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ላሉ የከተማ ነዋሪዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ።
Next articleበዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የታየውን አንጻራዊ ሰላም ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ።