በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ላሉ የከተማ ነዋሪዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ።

43

ባሕር ዳር: ጥር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ በባሕር ዳር ከተማ ለሚኖሩ ምጣኔ ሃብታዊ ችግር ላለባቸው ወገኖች የምግብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ወጣት ጽጌ ሞላ የባሕር ዳር ነዋሪ ነው። አካል ጉዳተኛ ሲኾን በጫማ ጽዳት ሥራ ቤተሰቦቹን ያሥተዳድራል። ”የኑሮ ውድነቱ የከፋ ነው፤ በዚህ ጊዜ ድጋፍ በመደረጉ ደስ ብሎኛል” ብሏል። ድጋፉ ቀጣይነት ቢኖረው ብሏል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ውስጥ ልብስ በማጠብ የምታሳድገው ታዘበች ገነቱ አንዷ ናት። ”ዛሬ ላይ ለልጅ ዳቦ መግዣ አሥር ብር በጠፋበት ጊዜ ቀይ መስቀል ስለደገፈን አመሰግናለሁ” ብላለች። “በከተማ ሴፍቲኔት ተጠቃሚ ስላልሆንኩ ችግር ላይ ነበርኩ፤ የቀይ መስቀል ድጋፍ ስላገኘሁም አመሰግናለሁ” ስትል ገልጻለች።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የሻምበል ዋለ የሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች ሲያጋጥሙ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርገው ቀይ መስቀል አሁንም በኑሮ ውድነት ለተቸገሩት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች እየደገፍን ነው ብለዋል።

ድጋፉ የተገኘው ከኦስትሪያ ቀይ መስቀል ማኅበር መኾኑን እና ለ1 ሺህ 600 ምጣኔ ሃብታዊ ችግር የተጋለጡ የከተማው ነዋሪዎች የምግብ ዱቄት እና ዘይት ድጋፍ መደረጉንም ገልጸዋል። ድጋፉ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ዋጋ እንዳለውም ገልጸዋል።

የተደረገው ድጋፍ በቂ አለመኾኑን እናውቃለን፤ ነገር ግን ያገኘነውን አካፍለናል፤ ይህንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ኀላፊው ተናግረዋል። ሌሎች ድርጅቶችም ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፍትሐነገሥት በዛብህ ቀይ መስቀል በተለያዩ ችግሮች ኅብረተሰቡን ሲደግፍ እንደነበር ገልጸዋል። ዛሬም የከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ የከተማ ነዋሪዎች ድጋፍ በማድረጉ አመስግነዋል። በከተማው ውስጥ በርካታ ወገኖች በድህነት እየተቸገሩ መኾኑን ጠቅሰው ሌሎች በጎ አድራጊ ድርጅቶችም መሰል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ከምዝበራ ማዳን መቻሉ ተገለጸ።
Next articleባሕርዳር ከተማ ከንግድ ባንክ ተጠባቂው የፕሪሜየር ሊግ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።