
ባሕር ዳር: ጥር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ከምዝበራ ማዳን መቻሉን የፌዴራል ሥነ – ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ አስቸኳይ ሙስና መከላከል መሪ ሥራ አስፈፃሚ ገዛኽኝ ጋሻው በስድስት ወራት ውስጥ የተካሔደውን አስቸኳይ የሙስና መከላከል ተግባር በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ 231 አስቸኳይ የሙስና መከላከል ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።
በመከላከል ተግባሩ ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብና ከ 21 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ የገጠር እና የከተማ መሬት ከምዝበራ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።
በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራው በምዝበራ ከተያዘው ሀብት ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኅብረተሰቡ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን በመስጠት ረገድ የነበረው ሚና የሚመሰገን እንደነበር ጠቁመዋል። በቀጣይም በፀረ ሙስና ትግሉ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!