
ባሕር ዳር: ጥር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፉት አራት ዓመታት ሁለት ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች የቡና ምርት የላኪነት ፍቃድ ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ገልጿል።
ከ100 በላይ አርሶ አደሮችም ምርታቸውን በቀጥታ ለውጪ ገበያ እየላኩ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው። የባለሥልጣኑ የድህረ ምርት ዝግጅት መሪ ሥራ አሥፈጻሚ መሐመድኑር አባጨብሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት ባለፉት አራት ዓመታት 1 ሺህ 996 አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለውጪ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ የቡና ምርት የላኪነት ፍቃድ ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል።
የቡና ግብይት ሰንሰለቱን ከማሳጠር አንጻር ሁለት ሄክታር እና ከዛ በላይ የቡና ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች በቀጥታ ከላኪዎች ጋር ተገናኝተው እንዲሠሩ እየተደረገ ሲኾን የበለጠ ውጤታማ እንዲኾኑ ሰፊ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የቡና ላኪነት ፍቃድ ከወሰዱት አርሶ አደሮች መካከል ከ100 በላይ የሚኾኑ ቡናቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ እየላኩ መኾናቸውን ገልጸዋል። አርሶ አደሮቹ የተመቻቸውን ዕድል ተጠቅመው ሕይዎታቸውን ከመቀየር ባለፈ ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉም አመላክተዋል።
ባለሥልጣኑ ባለፉት አራት ዓመታት የማሻሻያ ሥራዎችን መሥራቱን ጠቅሰው የግብይት ሥርዓቱን በማዘመን፣ የቡና ምርት ጥራትን በማስጠበቅ እና ምርቱ ላይ እሴት መጨመር በመቻሉ ጥሩ መሻሻሎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ቡናን ጨምሮ ምርታቸውን ለውጪ ገበያ ለሚልኩ ላኪዎች የምርት ዝግጅት፣ የጥራት፣ የእሴት ጭመራ እና የብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የዓለም የቡና ገበያ ተለዋዋጭነትን መሠረት በማድረግ ተጨማሪ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ወደ ቻይና፣ ኢንዶኔዢያ እና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የማስፋት ሥራ እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!