
ባሕር ዳር: ጥር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መተግበር የጀመረው በዚህ ዓመት ነው።
በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በዚህ ዓመት ይተግበር እንጅ የማስተማሪያ መጽሐፍት አለመሟላታቸው በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው በጋዝ ጊብላ ወረዳ የቤላ አምባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ተናግረዋል።
ተማሪ አስካል ሸጋው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ስትኾን የመጽሐፍት እጥረት በመኖሩ በውጤቷ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድርባት ሰግታለች። የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪው የቆዬ ተስፌ “አዲሱ መጽሐፍ ሳይደርሰን ሁለተኛ ሲሚስተር ሊጀምር” ነው ብሏል፡፡ ተማሪው የመጽሐፍ እጥረቱ የሀገር አቀፍ ፈተና ዝግጅት ላይ ተጽእኖ መፍጠሩንም አብራርቷል፡፡
የቤላአምባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል መምህሩ ይበልጣል ገነቱ ትምህርት ቤቱ በጦርነቱ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት መጽሐፍ እንደሌለው አስረድተዋል፡፡ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር እኩል ተወዳዳሪ ተማሪ ለማፍራት የግብዓት አቅርቦቱ ሊሟላ ይገባል ብለዋል።
የቤላ አምባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አማረ አጥናፉ በዚህ ዓመት ትምህርት ቤቱ 176 ተማሪዎችን እንደሚያስፈትን ገልጸዋል፡፡ የመጽሐፍት እጥረቱ በውጤቱ ላይ ተጽእኖ እንዳይኖረው ያላቸውን ስጋትም ተናግረዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሰይፉ ሞገስ ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በቂ መጽሐፍትን እንዳሠራጩ ገልጸዋል። ለ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በዚህ ሳምንት ለሁለት ወረዳዎች ከ40ሺህ በላይ መጽሐፍትን አሰራጭተናል ብለዋል።
ለቀሪ ትምህርት ቤቶችም ከዘገየ እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ለሁሉም ትምህርት ቤቶች መጽሐፍቱን እንደሚያሰራጩም ነው ያብራሩት። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!