ከግጭት አዙሪት በመውጣት ሁሉም ለሰላም እንዲሠራ ተጠየቀ።

26

ደብረ ታቦር: ጥር 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ በክምር ድንጋይ ከተማ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሚመለሰው በሰላም እና በምክክር መኾኑ ተነስቷል። በችግሩ ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውም ተመላክቷል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች መፍቻው አንድነት እና ሰላም ስለመኾኑ ተገልጿል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለሰላም ዘብ መቆም ይገባቸዋልም ነው የተባለው።
የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንበር ክፈተው ሰላም ከሌለ ለሁሉም ነገር አስቸጋሪ ነው ብለዋል። እውነታውን ከሃሰቱ እየለዩ መታገል እንደሚገባም አመላክተዋል።

የተሳሳተ ነገር ይዞ በሕዝብ መካከል መግባት ችግሮችን ያባብሳል እንጂ መፍትሔ አያመጣም ነው ያሉት። ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች የእኛም ጥያቄዎች ናቸው፤ ጥያቄዎቹ ግን በአንድ ጀንበር የሚፈቱ አይደሉም፤ ጥያቄዎቹ ሁሉን በሚያግባባ መንገድ እንዲፈቱ መታገስ ይገባል ብለዋል።

ጥያቄዎችን ለማስፈታት ሌሎች ኢትዮጵያውያን የእኛን ጥያቄ እንዲረዱት እና እንዲይዙት ማድረግ ይገባል፣ ጥያቄዎችን በአንድ ጊዜ እፈታለሁ ብሎ መነሳት አስቸጋሪ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል። የሌሎችንም እገዛ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን በጥበብ መፍታት ይገባል ነው ያሉት።

የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች አመራሩ አሳልፎ እንደሚሰጥ አድርጎ መቁጠር ስህተት ነው ያሉት ኀላፊው ጥያቄዎችን በእርቅ፣ በሰላም እና በውይይት መፍታት ይገባልም ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ዋልታና መከታ ነው ብለዋል፡፡

የወጡ ልጆች ይመለሱ፣ ሰላምን መርጠውም ወደ መደበኛ ሥራቸው ይመለሱ፣ ሰላምን አረጋግጠን ወደ ልማት መመለስ ይገባናል ብለዋል። ጥያቄ አለኝ የሚል ሁሉ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እና እንዲፈቱ መሥራት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ በግጭት ውስጥ የኖረ ማኅበረሰብ ብዙ ነገር እንደሚያጣ አመላክተዋል። የሃሳብ ልዩነት ሊኖር ይችላል፣ የሃሳብ ልዩነትን በሰለጠነ አግባብ መፍታት ይገባል ነው ያሉት። የማኅበረሰቡ ሃሳብ ሰላምን ማዕከል ያደረገ መኾን እንደሚገባውም አመላክተዋል።

አርሶ አደሮች ምርታቸውን እንዳያሳድጉ የአርሶ አደሮች የማዳበሪያ አቅርቦት እየተዘረፈ መኾኑንም ገልጸዋል። ትውልድ ሳይማር እንዲቀር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ እየተደረገ መኾኑን ያነሱት ዋና አሥተዳዳሪው ይሄን አካሄድ ማስተካከል ይገባል ነው ያሉት።

በሰላም እጦት በምርት መቀነስ የሚሰቃየውን ሕዝብ ማገዝ ሲገባ በግጭት ውስጥ እንዲኖር የሚሠሩ ኃይሎች ከጥፋታቸው መመለስ አለባቸው ብለዋል።
በግጭቱ ምክንያት ችግር እየደረሰበት ያለውን ማኅበረሰብ ከችግር ለማውጣት የሰላም ባለቤት መኾን ይገባልም ብለዋል። ሰላምን ማስጠበቅ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መኾኑንም አንስተዋል። በዞኑ የነበረው የጸጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መኾኑን አመላክተዋል።

አካባቢው በሕልውና ጦርነቱ ወቅት ከደረሰበት ችግር ሳያገግም በክልሉ በተፈጠረው ችግር አካባቢው ችግር ውስጥ መቆየቱንም አመላክተዋል።
በዞኑ በተሠራው ሥራ አብዛኞቹ የመንግሥት ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውንም አንስተዋል። የተፈጠረውን ችግርም በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ይገባል ነው ያሉት።

መንግሥት የሚጠበቅበትን እንደሚሠራም ገልጸዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የአካባቢው የሰላም ሁኔታ እንዲሻሻል አይተኬ ሚና መጫወቱንም ተናግረዋል። የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ሕዝብን ከመንግሥት ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

መንግሥት ለሰላም አማራጭ በሩ ክፍት ነው፣ በግጭት ውስጥ ያሉ ኃይሎች ስለ ሰላም መግባት ይገባቸዋል፣ ለሰላም እምቢ በሚሉ ኃይሎች ግን ሕግ የማስከበር እርምጃው ይቀጥላል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ መከላከያን መውደድ ግድ ይለዋል፣ መከላከያ ሀገር የሚያፀና ነውም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo, Amajjii 15/2016
Next articleየ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጽሐፍትን በሁሉም ትምህርት ቤቶች እንደሚያሰራጭ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።