“በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች መንግሥት አፋጣኝ ሰብአዊ እርዳታ እያደረሰ ነው” የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት

14

አዲስ አበባ: ጥር 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መንግሥት ከተለየዩ አካላት ጋር በመተባበር አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወገኖች እርዳታ ማድረሱን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ ለሰብዓዊ እርዳታው በሦስት ተከታታይ ዙሮች 15 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 40 በመቶውን የፌዴራል መንግሥት 60 በመቶውን ደግሞ የዓለም ባንክ እንደሸፈነው ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በድርቅ እና በተለያዩ ምክንያቶች ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከ9 ሚሊዮን በላይ ወገኖች ተለይተው እርዳታውን ከጥር እስከ የካቲት ለማድረስ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ለእነዚህ ወገኖች የሚደርሰውን እርዳታ የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመው ለዚህም 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በፌዴራል መንግሥት በኩል አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ያልተቋረጠ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ አየተሠራ መኾኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ የክልል መንግሥታትም የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ለእነዚህን ወገኖች ለመድረስ የእርዳታ ድርጅቶችን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም ለማምጣት ወሳኙ እና አዋጩ ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው” የክምር ድንጋይ ነዋሪዎች
Next articleምሁራን ሀገራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ ሚናቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳሰበ።