
ባሕር ዳር: ጥር 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ በክምር ድንጋይ ከተማ በወቅታዊ ጉዳዮች የሕዝብ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንበር ክፈተው፣ በመከላከያ ሠራዊት የ503ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ደምሰው አንተነህ፣ የ92ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ጀዋር ዴኮን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የክምር ድንጋይ ነዋሪዎች መንግሥት ሰላምን ማስከበር ይገባዋል ብለዋል። ሕዝብ በሰላም እጦት መኖር እንደሚበቃውም አመላክተዋል። በወንድማማቾች ግጭት ንፁሐን እየተጎዱ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የሰላም ሁኔታው እልባት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ማኅበረሰቡ በችግር ውስጥ መቆየት እንደሰለቸውም ተናግረዋል። መፍትሔው ከመንግሥት እጅ ላይ መኾኑንም አንስተዋል።
የሕዝብ ጥያቄ ግልጽ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ በፍትሐዊነት እና በእኩልነት እንኑር ስለማለቱም አብራርተዋል። የአማራ ሕዝብ በሰሜኑ ጦርነት ከደረሰበት ጉዳት ሳያገግም ለሌላ ችግር መዳረጉንም አንስተዋል።
መንግሥት ግጭት ከመከሰቱ አስቀድሞ ሕዝብን ማወያየት እና ለችግሮች መፍትሔ ማበጀት ይገባዋልም ብለዋል።
ሕዝብን የሚዘርፉ፣ የሚያግቱ እና የሚያንገላቱ ለሕዝብ የማይጠቅሙ እና የሕዝብን ጥያቄዎች የማያስፈቱም እንደኾኑ ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ መኖር ነውም ብለዋል።
ችግሮችን በውይይት መፍታት አዋጩ መንገድ መኾኑንም ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ የመከላከያ ሠራዊትን ብሉልን ጠጡልን የሚል እንጂ በክፋት የሚያይ አለመኾኑንም ተናግረዋል። ሀገር የሚረከብ ትውልድ በግጭት እየተጎዳ ነው፣ ችግሮችን በሰላም ፈትቶ ለሕዝብ ሰላም መስጠት እና ሀገር የሚረከብን ትውልድ መጠበቅ ይገባልም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሰላም ሠርተው የሚበሉበት ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባም አንስተዋል። የአማራ ሕዝብ ዓላማ ኢትዮጵያን ማጽናት መኾኑንም ተናግረዋል።
ሰላም ለማምጣት ወሳኙ እና አዋጩ ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው፣ ቁጭ ብላችሁ ተነጋገሩ እና ሰላም እንሁን፣ በሰላም ሥራችን እንሥራ፣ የኑሮ ውድነቱ ለመኖር አስቸግሮናል ነው ያሉት።
ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ለሰላም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል። ሰላም የሁሉም ነገር መፍትሔ እንደኾነ ከመናገር ባለፈ ለሰላም መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
ከአሁን ቀደም የነበሩ ስህተቶችን በማረም በሰላም መኖር ይገባልም ብለዋል። ለትውልድ የሚያስብ፣ ትውልድን የሚያሻግር ሀሳብ እና መሪ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!