የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ እንደወትሮው በተሳካ መንገድ ለማከናወን ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

27

አዲስ አበባ: ጥር 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ.ር) ወቅታዊ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል እና በጋራ ተጠቃሚነት መርኅ የምትሠራውን የመልማት ተግባር በጠንካራ ዲፕሎማሲ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በቀጣናው በጋራ እንልማ ብሎ ለመጣ ሀገር እና አካል ሁሉ ለመወያየት እና ለድርድር ዝግጁ መሆኗንም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ከፍትሐዊነት ውጭ ከየትኛውም አካል ሁኔታዎችን ለማጋጋል የሚወጡ መግለጫዎች ለማንም የማይጠቅሙ እና ለውጥ የማያመጡ መኾናቸውን አስረድተዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ እንደወትሮው በተሳካ መንገድ ለማከናወን ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ የካቲት 9 እና 10/2016 ዓ.ም ይካሄዳል። ለስብሰባው መንግሥት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች በተጨማሪ ኅብረተሰቡም የሚጠበቅበትን ኀላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሣይንስ ሙዚየም በመካሄድ ላይ የሚገኘው የዲፕሎማሲ ሣምንት በተቋማት፣ በዲፕሎማቶች እና በማኅበረሰቡ እየተጎበኘ መቀጠሉ አንዱ የዲፕሎማሲ ስኬት ስለመሆኑም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኽምጠ ዊከ ጋዜጠ ፡ ጥር 15/2016 ዓ.ስ
Next article“የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን በስኬት ለማስተናገድ በቂ ዘግጅት ተደርጓል” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት