
ባሕር ዳር: ጥር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የወልድያ ከተማ አሥተዳደር የ2016 ዓ.ም የተፈጥሮ ሃብት ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብርን በአደንጉር ቀበሌ አካሂዷል።
በከተማ አሥተዳደሩ 15 ተፋሰሶች መኖራቸውን የጠቀሱት የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ደስታ ሞላ ተፋሰሶቹ 8 ሺህ 10 ሄክታር መሬት የሚሸፍኑ ሲኾን 2 ሺህ 600 ሄክታሩ በደን የተሸፈነ ነው ብለዋል።
ሌሎች ነባር ተፋሰሶች ላይም በየዓመቱ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል። በዚህ ዓመት በአምስት ተፋሰሶች 2 ሺህ 699 ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን ነው መምሪያ ኀላፊዋ የገለጹት።
እነዚህን የለሙ ተፋሰሶች ለሥራ እድል ፈጠራ በመጠቀም በንብ ማነብ ለሚሰማሩ ወጣቶች ከተማ አሥተዳደሩ 10 ሚሊዮን ብር መድቦ ወደ ሥራ ለማስገባት ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
በወልድያ ከተማ ግብርና መምሪያ የ07 ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሀም ማስረሻ አርሶ አደሩ የተፋሰስ ልማትን ፋይዳ በተግባር በመረዳቱ ያለ ቀስቃሽ እየሠራ መኾኑን ገልጸው በአካባቢው ያለው የተፈጥሮ ሃብት ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደጉን ነግረውናል።
አሚኮ በልማት ሥራ ላይ አግኝቶ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች በበኩላቸው ከዚህ በፊት አባቶቻቸው በሰፊ መሬት ብዙ ምርት ያስገቡ እንደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ እነሱ በተፋሰስ ልማት ከትንሽ መሬት የተሻለ ምርት እያገኙ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በመኾኑም ጥቅሙን በመረዳታቸው ዓመታዊ የተፋሰስ ልማቱን በወል ከመሥራት ባሻገር በተናጥል የማሳቸውን አቅራቢያ ተፋሰስ ያለማቋረጥ እየተንከባከቡ መኾኑን ነግረውናል።
ዘጋቢ፦ ካሳሁን ኃይለሚካኤል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!