የአማራ ሕዝብ ለባሕል እና እሴቶቹ ዳብረው መቀጠል የሚያደርገውን አበርክቶ አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጠየቀ፡፡

25

ባሕር ዳር፡ ጥር 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ክረምቱ አልፎ የበጋው ፀሐይ ከመምጣቱ በፊት መሸጋገሪያ የኾነው ከሕዳር እስከ መጋቢት ድረስ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት በስፋት እና በድምቀት ይከበራሉ፡፡ በአማራ ክልልም በየአካባቢው በተለያዩ ስያሜዎች የሚታወቁ በዓላት በሰላም መከበራቸውን ቀጥለዋል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት፣ ከተራ፣ ጥምቀት፣ ቃና ዘገሊላ፣ አቡነ ዘረአብሩክ እና የግሽ ዓባይ ክብረ በዓል፣ ሰባር ጊዮርጊስ፣ አስተርዕዮ ማርያም፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል እና የመርቆሪዮስ በዓላት በአማራ ክልል ጥርን ከሚያደምቁ በዓላት መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ በሁሉም የአማራ ክልል እና የሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ በጉጉት እና በደስታ ይከበራሉ፡፡

የዘንድሮ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት በሰላም መከበራቸው የማኅበረሰቡን ጨዋነት የሚያመላክቱ መኾናቸውን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል፡፡ የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አበበ እንቢአለ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሰጡ ማብራሪያ፤ የአማራ ክልል ሕዝብ ለባሕሉ እና ለእሴቶቹ ባለው ቀናኢነት በዓላቶቹን ሲያከብር ያሳየው ጨዋነት የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡

በዓላቶቹ የአማራ ሕዝብ ማንነት መገለጫ ዕሴቶች በመኾናቸው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መንግሥትም ትኩረት እንደሚሰጥ ነው አቶ አበበ የገለጹት፡፡ ዘንድሮም በዓላቱ ሲከበሩ በተለያዩ ሁነቶች እንዲታጀቡ እና እንዲጠናከሩ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ በባሕል እሴቶች ላይ ውይይት፣ አውደ ርዕይ፣ የጎዳና ላይ ትዕይንት፣ የሽምግልና እና የጀግንነታ ታሪኮች ዝክር፣ የንጉስ እራት ግብዣ፣ የኢንቨስትመንት ፎረም፣ የባሕል ኤግዚቢሽን፣ የጀልባ ጉዞ እና የታንኳ ቀዘፋ ውድድር በማድረግ እየተከበሩ እንደሚቀጥሉ ነው አቶ አበበ ያብራሩት፡፡

በሁነቶቹ ለሀገር ውስጥም ለውጪም ጎብኚዎችን ባህልና ታሪክን የማስተዋወቅ እና በቆይታቸው ግብይት በመፍጠር የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ከተሞችን ጨምሮ አካባቢን በማጽዳት እና በማስዋብ ሳቢና ማራኪ የማድረግ፣ አካባቢዎችን የሚያስተዋውቁ መረጃ ሰጪ አሠራሮችን በማጠናከር እንግዶች እንዲቆዩ የሚያስችል ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በዓላትን በመከባበር እና በሰላም እያከበረ መኾኑን የገለጹት አቶ አበበ ፤ በዓላትና የሕዝቡ በመኾናቸው ተጠቃሚውም ራሱ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዓላት ለአካባቢው በሚፈጥሩት ተደራሽነት እንግዶች ስለ አካባቢው ባሕል እና ታሪክ ከማወቃቸውም በተጨማሪ ገቢ የማስገኘት ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ሲተባበር በርካታ መልካም ነገሮች መሥራት እንደሚቻል የታየበት ነውም ብለዋል፡፡ በዚህም ወጣቶችን፣ የሆቴል ማኅበራትን፣ አስጎብኝ ድርጅቶችን እና የሃይማኖት አባቶችን አመሥግነዋል፡፡

ሃይማኖታዊም ኾኑ ባሕላዊ በዓላት ሃብት እና እሴታቸው ለኅብረተሰቡ በመኾኑ ትውፊታቸውን ጠብቆ ለማቆየት የሁሉም ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ የእንግዶችን ሰላም እና ደኅንነት በመጠበቅ፣ አላግባብ ዋጋ ባለመጨመር፣ እንዲሁም ስለ ባሕል እና እሴቶች ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ገጽታን መገንባት፣ የሥራ ዕድል መፍጠር እና ገቢን ማሳደግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት 10 ሺህ 491 የውጪ እና 4 ሚሊዮን 619 የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች የተለያዩ ቦታዎችን መጎብኘታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ ፤ ከዚህም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ በጥር ወር የሚከበሩ በዓላትን ለመታደምም 534 የውጪ ቱሪስቶች ወደ አማራ ክልል መግባታቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ የሚከበሩ በዓላትም እንደ ከዚህ በፊቱ በሰላም እና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ተከብረው እንዲጠናቀቁ ማኅበረሰቡ ትብብሩን እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመውጫ ፈተና እስከ ጥር 20/2016 ዓ.ም መራዘሙን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next articleየብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ገለጸ።